በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ”ማንነት ተኮር” ጥቃት ከ20 በላይ ንጹሃን ተገደሉ

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ግንቦት 25 ፈጸመው በተባለ “ማንነት ተኮር” ጥቃት ከ20 በላይ ንጹሃን እንደተገደሉ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ሰሞኑን በመንግሥት ወታደሮችና አማጺው ቡድን መካከል ተከታታይ ውጊያዎች እየተካሄዱ ስለመኾኑ ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።

በቄለም ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መኾኑን፣ ነዋሪዎችም ከቤት ለመውጣት እንደተቸገሩና ውጊያው በተለይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ በሚገኝበት ሰዮ ወረዳ እየተካሄደ እንደኾነ ተናግረዋል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን ቢሎ ቦሼ፣ ሌቃ ዱለቻ እና ኑኑ ቁምባስን ወረዳዎችም በተለይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፖች በሚገኙባቸው ጅማቴ እና አዳሚን በተባሉ አካባቢዎች ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ እንደኾነ ተሰምቷል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረትና ጀልዱ ወረዳዎች እንዲኹም በሰሜን ሸዋ፣ በጉጂ፣ በምሥራቅ ሸዋና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች ግጭት ሲካሄድ መሰንበቱ ታውቋል።