በድርድር ወቅት የተገባላቸው ቃል ባለመፈጸሙ ለችግር መጋለጣቸውን የአዲኃን ታጋዮች ተናገሩ፡፡

በድርድር ወቅት የተገባላቸው ቃል ባለመፈጸሙ ለችግር መጋለጣቸውን የአዲኃን ታጋዮች ተናገሩ፡፡

አዴፓ በበኩሉ በስምምነቱ መሰረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Image may contain: 1 person, outdoor

(አብመድ) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ታጋዮች ከስምንት ዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ የነበረውን ስርዓት በመቃወም ለነፃነት ትግል በኤርትራ በርሃ ውስጥ በትግል ቆይተዋል፡፡ ሰላማዊ የትግል ጥሪውን መሰረት አድርጎም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡

አዴኃን 324 የሰራዊት አባላቱን ይዞ ነው ወደ ሀገር የገባው፡፡ የአዴኃን ታጋይ ተስፋሁን አለምነህ የ286ቱን የሰራዊት አባላት ፍላጎትና ጥቅም ባላካተተ መንገድ ከአዴፓ ጋር ተደረገ የተባለው ውህደት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ የአዴኃን ታጋዮች ወደ ሀገር ውስጥ ከገባን በኋላ ነባር አመራሮቻችን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በአግባቡ ሊመሩን አልቻሉም፤ የድርጅቱ ጉባኤ እስኪካሄድ ድረስ በጊዜያዊነት ከአመራርነት አግደናቸው ነበር ነው ያሉት፡፡ ትናንት ደግሞ ጉባኤውን በባሕር ዳር ከተማ ነባር አመራሮቹ በሌሉበት አካሂዷል፡፡

ታጋይ ጋሹ ጥሩነህ እና ታጋይ ጌታሁን ዋለ በጉባኤው ከተሳተፉት መካከል ናቸው፡፡ የክልሉ መንግሥት ኤርትራ ድረስ ሄዶ ባደረጉት ድርድር 41 ነጥቦች ላይ ቃል ቢገባላቸውም እስካሁን ድረስ ምንም ተግባራዊ አለመደረጉን ነው የተናገሩት፡፡ ታጋዮቹ ለስምንት ዓመታት ከትውልድ ቀያቸው ርቀው በመቆየታቸውም ለቤተሰብ ጥገኝነት መዳረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት ለአብመድ በስልክ ማብራሪያ የሰጡን በቀድሞው አዴኃን ውስጥ የድርጅቱ የፖለቲካና ውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ታጋይ ደነቀው ባያብል እና የድርጅቱ መረጃና ደህንነት መምሪያ ኃላፊ ታጋይ ፍፁም አየነው አዴኃን ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) ጋር ውህደት መፈጸሙን ነው ያረጋገጡት፡፡
እንደ ታጋዮቹ ማብራሪያ በመተዳደሪያ ደንቡ በግልፅ በተቀመጠው መሰረት ከየትኛውም ድርጅት ጋር አዴኃን ጥምረት ወይም ውህደት የማድረግ ፍላጎት ቢኖረው ጉዳዩን የመፈፀም ስልጣን የተሰጠው ለስራ አስፈፃሚው አካል ነው:: አሁን አዴኃን የሚባል ድርጅት አለመኖሩንና ታጋዮቹም ከመንግስት ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት በክልሉ ልዩ ኃይል እና በተለያዩ ቦታዎች በመግባት የክልሉን ህዝብ እንዲያገለግሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ወደ ስራ ያልተሰማሩ ታጋዮችንም ከአዴፓ ጋር በመነጋገር አገልግሎት መስጠት በሚችሉባቸው የተለያዩ ቦታዎች እንዲገቡ፣ ካልተቻለ ደግሞ ራሳቸውን ለማቋቋም እንዲችሉ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡ አዴኃን ውህደት ፈጽሟል፤ በቀድሞ የአዴኃን አመራሮች አሁን ተደረገ የሚባለው ጉባኤ ተቀባይነት የሌለው እና በአዴኃን ስም የሚደረግ ሌላ እንቅስቃሴ ነውም ብለዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ‹‹ድርድርና ውህደት ልዩነት አላቸው፤ ኤርትራ በረሃ ውስጥ እያሉ አዴፓ ወደ አስመራ በማቅናት የአዴኃን ታጋዮች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሀገራቸው በመግባት እንዲታገሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል፤ በስምምነቱ መሰረትም ወደ ሀገር ገብተው የተሃድሶ ስልጠና ወሰደው ክልሉን ሊደግፉ በሚችሉበት ማንኛውም ቦታ ለማሰማራት ጥረት እየተደረገ ነው›› ብለዋል፡፡ ቀሪዎችን ደግሞ እራሳቸውን ለማቋቋም እንዲችሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
በውህደቱ ወቅት ቅሬታ ያነሳ ታጋይ እንዳልነበረና የአዴኃንንም ሆነ የአዴፓን ውህደት የፈፀሙትም የየድርጅቶቹ መሪዎች መሆናቸውን አቶ ምግባሩ ነግረውናል፡፡

ቁጥሩ ይብዛም ይነስም በውህደቱም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቅሬታ ያለው የአዴኃን ህጋዊ ታጋይ ካለ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት አዴፓ ዝግጁ መሆኑንም የጽፈት ቤት ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡