ኤርትራዊያኑ ከ 21 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ትተውት የሄዱትን የዕቁብ ብር ከ50 በመቶ ወለድ ጋር ተረከቡ፡፡

(አብመድ)

ኤርትራዊው ከ21 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይጥሉት የነበረ የዕቁብ ብር ከ50 በመቶ ወለድ ጋር ጠብቋቸዋል፡፡

‹‹አደራ የበላ በመሬትም ሆነ በሰማይ እረፍት የለውም›› ይላሉ ኢትዮጵያውያን በልማዳቸው ስለአደራ አክባሪነታው ሲናገሩ፡፡ ሌባ እንኳ በአደራ የተሰጠውን እንደማያጎድል የሚታመንባት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ፡፡

ከዓመታት በፊት የተቃቀፉ ክንዶች በደራሽ የፖለቲካ ግጭት ተለያዩ፤ ወሰን ያልተበጀላቸው የአንዲት ሀገር ግዛቶች ድንበር ወስነው ሁለት ሀገር ሆኑ፡፡ ሐዘን እና ደስታቸው የጋራ የነበረ ጎረቤታሞች ተለያይተው ደኅንነታቸውን ላይጠያየቁ፣ ሲቸግራቸው አንዳቸው ለሌላኛቸው የቀን ማሳለፊያ ላያበድሩ፣ ልጅህን ለልጄ ላይባባሉና በሐዘን-ደስታቸው ላይገናኙ ተለያዩ፤ ኢትዮጵያውንና ኤርትራውያን፡፡

መንግሥታቱ በዓይነ ቁራኛ እየተያዩ ሲያስፈልጋቸውም ሞት እየተወራወሩ፣ ሕዝቦቹ ደግሞ በጎረቤት ሀገር በኩል እየተገናኙ ናፍቆታቸውን ለመወጣት እየሞከሩ ሁለት አስርት ዓመታትን አሳለፉ፡፡ ጃንሆይ ከመንበራቸው ሳሉ፣ እሳቸው ወደማይቀረው ዓለም ሲያልፉ፣ደረግ ስልጣን ሲቆጣጠር ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ሲያሻቸው ኤርትራ ሲፈልጉ ደግሞ ኢትዮጵያ ይኖሩ ነበር፡፡
ዓመታቱ የአንድ ሀገር ልጆች ሁለት ሀገር መሥርተውና ሁለት ሕዝቦች ሆነው በጥይት የተጨፋጨፉበት ነበሩ፡፡

ወንድም ወንድሙን ገድሏል፤ አቁስሏል፤ ማርኳል፡፡ ዜጎች ሀብት ንብረት ያፈሩበትን ቀየ ለቅቀው ተፈናቅለዋል፡፡ የዚህ ዕጣ ፋንታ ከደረሳቸው አባት አንዱን በባሕር ዳር አገኘናቸው፡፡ አቶ ፀሐዬ ኃይሉ ይባላሉ፡፡ በኤርትራ ግዛት ውስጥ ሰናዓፍ ከምትባል ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ እኝህ ሰው በዚሁ ተወልደው ባደጉበት ሀገር ደሀብ ጎይቶም የሚባሉ ሚስት አግብተው ሁለት ልጆችን ወለዱ፡፡ ሥራቸውም ንግድ ነበር፤ ከኤርትራ – ጨው ወደ ኢትዮጵያ ያመጣሉ፤ ከኢትዮጵያ ደግሞ እህል ወደ ኤርትራ እየወሰዱ ይነግዳሉ፡፡ ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማድረግ ወደ ባሕር ዳር መጡ፡፡

ማረፊያቸውን በጭስ ዓባይ አድርገው ሻይ ቤት በመክፈት ለጎብኝዎች እና ለአካቢቢው ኅብረተሰብ ሻይ በመሸጥ ኑሮ ጀመሩ፡፡ በሂደት ደግሞ ከጭስ ዓባይ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ተዛወሩ፡፡ ‹‹እኔ ባሕር ዳር ስገባ ባሕር ዳር ትንሽዬ ከተማ ነበረች፡፡ ወጣ ያሉ ቤቶች እና የሥራ ቦታዎች አልነበሩም፡፡ የደስ ደስ ቢኖራትም ትንሽ ነበረች›› ይላሉ አቶ ፀሐዬ ከረጅም ዓመት በኋላ የረገጧትን ባሕር ዳር ከቀደመው ጋር እያነጻጸሩ፡፡

አቶ ፀሐዬ ከወይዘሮ ደሀብ ጋር ባሕር ዳር ከተማ እያሉ አምስት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ያ! ቀደም ሲል ትተውት የነበረውን የንግድ ሥራም እንደገና ጀምረዋል፡፡ በኋላ ላይ አቶ ፀሐዬ ከወሮ. ደሀብ ጋር ተለያይተው በ1980ዎቹ አካባቢ ነዋሪነታቸውን በኢትዮጵያ ካደረጉ ሌላኛዋ ኤርትራዊት ወይዘሮ ሐረጓ አብርሃም ጋር ጋብቻ ፈጸሙ፡፡ ከእኒህ ሴትዮ ጋርም አራት ልጆችን በባሕር ዳር ከተማ አፍርተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹ኑሯችንም ሞታችን እዚሁ ነው፤ ሀገር ደህና ሰውም ጤና›› ብለው ይኖሩ ጀመር፡፡

ዘመንን ዘመን እየተካው ሲመጣ የሁለቱ ወንድማማቾች ጦርነት በባድሜ እና በአካባቢዋ ሲነሳ ‹‹እናንተስ የእኛ አይደላችሁም›› የሚል ትዕዛዝ ከመንግሥት አካላት ደረሳቸው እና ከሚወዱት እና ለዘመናት አብረውት ከኖሩት ኅብረተሰብ ተለይተው ወደ ኤርትራ ሄዱ፡፡ አቶ ፀሐዬ 30 ዓመታትን ያክል በባሕር ዳርና አካባቢዋ ተቀምጠዋል፡፡ ኑሯቸው በቀሌ 12 በመንግሥት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ የግላቸውን ቤት በሽምብጥ ክፍለ ከተማ ገንብተውም ነበር፡፡ ነገር ግን በአዲሱ ቤታቸው ለመኖር አልታደሉም፤ ጥረው ግረው የሰሩትን ቤት አንድ ቀን እንኳን ሳያርፉበት ነበር ከኢትዮጵያ የወጡት፡፡

አቶ ፀሐዬ በባሕር ዳር ከተማ ሲኖሩ አባ ግዛቸው ተሰማ የሚባሉ አባት ከሚመሩት እና ከመሠረቱት ዕቁብ ውስጥ በየሳምንቱ ዕቁብ ይጥሉ ነበር፡፡ 32ሺህ ብር ዕቁብ እንደጣሉ በድንገት የኢትዮጵያን ምድር ለቀቁ፡፡
የሁለቱ ሀገራት ፀብ ‹‹ዛሬ ይረግብ ወይስ ነገ?›› በማለት ሲጠባበቁ አባ ግዛቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ነገር ግን አደራ በልተው አላረፉም፤ የሰውን ንጹሕ ገንዘብ አደራ ‹‹ለቀሪ ሰዎች እንድትሰጫቸው›› በማለት ለሚስታቸው ኑዛዜ አስቀምጠው ነበር ያለፉት፡፡ ባለቤታቸውም ለአቶ ዘመነ አባተ እና ለአቶ ተስፋ እስከዚያ ገንዘቡን አስረከቡ፡፡ አቶ ዘመነ የዕቁቡ ዋና ፀሐፊ፣ አቶ ተስፋ ደግሞ ሊቀ-መንበር ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡

እኝህ ሁለት ሰዎች ‹‹አደራ ከሰማይ ይርቃል፤ ቢበሉት እኳን ያንቃል›› በማለት ገንዘቡን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስቀምጠው የዕርቅ ዘመን መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ‹‹ዛሬ፣ ነገ…›› ሲሉ 21 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የመገናኛቸው ነገርም እየራቀ ሄደ፡፡ እምነታቸው ግን አልተሸረሸረም፤ ነገም ሌላ ቀን እንደሆነ በማሰብ ተስፋ በማድረግ በታማኝነታቸው ቀጠሉ፡፡

ተስፋ አለመቁረጥ፣ ቃልም አለመሻር መልካም ነው እና ተስፋ ያረጉት ዘመን ደርሶ ገንዘቡን ለባለቤቱ ከ21 ዓመታት በኋላ አስረከቡ፡፡ ከዓመታት በፊት ያስገቡት ገንዘብም ወደ 48ሺህ 4መቶ 62 ብር ከ60 ሳቲም ከፍ ብሎ በባንክ ቤት ተገኘ፡፡ ገንዘቡን ባንክ ላይ አስቀምጠው የመገናኛቸውን ቀን ሲጠብቁ የነበሩትን አቶ ዘመነ ‹ይህ ሰላም ባይመጣ ገንዘቡ እንዴት ይሆን ነበር?› ብለን ጠየቅናቸው፡፡ ‹‹ስልጣን አላፊ ነው፤ ፀብም ጊዜያዊ ነው፤ ፍቅር ግን ዘላለማዊ ነው፤ ‹ስዩመ እግዚያብሔር› ሲባሉ የነበሩት ኃይለሥላሴ ከስልጣን ሲወርዱ አይተን፣ ዓለም ሲፈራው የነበረው ደርግ ከስልጣን ሲወርድ ተመልክተን፣ ይህ ሥርዓት አልፎ ከዘመዶቻችን ጋር እንደምንገናኝ ፅኑ ተስፋ ነበረን›› አሉ፡፡

ያሉት ደርሶ አቶ ፀሐዬ ከባለበቤታቸው ከወሮ. ሐረጓ ጋር በመሆን ይኖራል ብለው አስበውት የማያውቁትን ገንዘብ ተረከቡ፡፡

ቤታቸውንም እንደሚሰጧቸው ቃል እንደገቡላቸው ነግረውናል፡፡ አቶ ፀሐዬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥለዋቸው የተሰደዱትን ልጆቻቸው ለማግኘት በባዕድ ሀገር በኩል ያደርጉት የነበረውን ጥረት ሲያስታውሱ እንባ ይተናነቃቸዋል፡፡ ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ሲገናኙ የነበሩት ወንድማማች ሕዝቦች ጥል በሚሉት ግድግዳ መንገዳቸው ተዘግቶ ዓመታትን አሳለፉ፡፡

ዛሬም ሌላ ታማኝነት! ትናንት ደብረ ማርቆስ ላይ ቤትና ንብረት ተጠብቆ ለኤርትራውያን ተመልሷል፤ ቀጥሎም ባሕር ዳር ላይ ቤትን ጠብቆ ከማቆየትና ከማስረከብ በተጨማሪ ለ21 ዓመታት የተሰበሰበላቸውን የቤት ኪራይ ጭምር ተረክበዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሌላ ታማኝነትና ታማኝ ሰዎችን አገኘን፡፡