በሕግ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ‹‹በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት›› በማለት ሥራን የሚመሩት ባለስልጣናትና የማያነቡት ተቋሞቻቸው

የመንግሥት ተቋማትና አመራሮች ሳይናበቡ ሲቀሩ በአገልግሎት ፈላጊዎችም ሆነ በአጠቃላይ ሕዝቡ ኑሮ ላይ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ስለተግባራቸው፣ ኃላፊነታቸውና ተጠያቂነታቸው በተቋቋሙበት ሕግ ተደንግጓል፡፡ አመራሮቻቸውም እንዴት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡና ስለሚኖርባቸው ተጠያቂነትም በሕጎች ውስጥ በሚገባ ሠፍሯል፡፡ በሕግ በተወሰነላቸው ጊዜ መሠረትም ዕቅዳቸውና አፈጻጸማቸው በሕግ አውጭ ምክር ቤቶች ይገመገማል፡፡ በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጪ አላግባብ ከተሰማሩም በሕግ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም ሥራቸውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ እንዲወጡ ድንጋጌ አለ፡፡ በዚህ መሠረት ተቋማትም ሆኑ አመራሮች እየተናበቡ ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው፡፡ በሕግ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ‹‹በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት›› በማለት ሥራን መምራት ፈፅሞ አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ ሲያጋጥም ሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው በቅንጅት ማስቆም አለባቸው፡፡

የአስፈጻሚው አካል የሆነው ካቢኔም ቢሆን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በተጠሪ ተቋማት በዘፈቀደ የሚከናወኑ ሥራዎችን መመርመር አለበት፡፡ ሁሉም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት በማንኛውም አሠራር መናበብ እንዳለባቸው ቁጥጥር ማድረግ አለበት፡፡ በየጊዜው ሲሰበሰብም ይህ ጉዳይ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለምሳሌ አገሪቱ ከውጭ ስለምታስገባቸው የተለያዩ ምርቶች በሕግ ከተወሰነው ውጪ፣ ማንም እየተነሳ ፈቃጅና ከልካይ መሆን እንደሌለበት በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱን በጀት የሚያዘጋጀው አካል እያለ ሌላው በማይመለከተው ጣልቃ እንዳይገባ መደረግ አለበት፡፡ በሌተር ኦፍ ክሬዲትም ሆነ በፍራንኮ ቫሉታ ስለሚገቡ ምርቶችም ሆነ ማሽነሪዎች በሕግ ከተደነገገ ውጪ ‹‹በልዩ ሁኔታ›› የሚባል አሠራር መቅረት አለበት፡፡ በሕግ የተፈቀደ መግባት ሲኖርበት፣ ያልተፈቀደ ደግሞ መቅረት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአግባቡ መናበብ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ዕርምጃዎቹ ሕጋዊ መሠረት ሊኖራቸውና በሚያሠሩ ደንቦችና መመርያዎች መታገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ አዋጅ ሲወጣ ከአዋጁ በተጨማሪ ማስፈጸሚያ ደንቦችና መመርያዎች በሁሉም ተቌማትና አመራሮች ሊከበሩ ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት ሕጉን ማስፈጸም የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነት ነው፡፡ ከሕጉ በተቃራኒ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ደግሞ ማስጠየቅ አለባቸው፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችም ሆኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በተመለከተ ሁሉም አሠራር ሕጋዊ መሠረት ሊኖረው ሲገባ፣ በዘፈቀደ ውሳኔ ኃላፊነትን ለመወጣት በሚል ምክንያት ብቻ ሕግ መጣስ ማስጠየቅ አለበት፡፡ ሕግን መሠረት ያደረጉ አሠራሮች ብቻ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ማናቸውም ተግባራት የሕግ መሠረት ከሌላቸው ሥራ ላይ ቢውሉም ተቀባይነት የላቸውም መባል ይኖርበታል፡፡ የዘፈቀደ ውሳኔ አገር ይጎዳል፡፡

በተደጋጋሚ ስለተቋማት ግንባታና ስለአመራሮቻቸው ጉዳይ ሲነሳ እንደ ቅንጦት ሊታይ አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዴት ውጤታማ ሆነ የሚለውን መመርመር ይገባል፡፡ አንገት ለአንገት ተያይዘው ከፍተኛ ፉክክር በሚደረግበት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትርፋማ ሆኖ፣ በዚህ ላይ በየዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት እያገኘ የቀጠለው ዝም ብሎ አይደለም፣ ከበፊት ጀምሮ በገነባው ተቋማዊ ጥንካሬ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮ ቴሌኮም እያሳየ ያለው ግስጋሴ እየተላበሰ ያለውን ተቋማዊ ጥንካሬ ያመላክታል፡፡ ስለተቋም ግንባታ ሲነሳ የሕግና ሥርዓት ጉዳይ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ተቋማትም ሆኑ አመራሮች በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ሲችሉ ውጤታማ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም ይገነባሉ፡፡ ለዘመኑ የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት ጥንካሬ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር በነበራቸው ውይይት ከተነሱላቸው አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሙስና ቅጥ ማጣት፣ ደንቦችንና መመርያዎችን ማስፈጸም አለመቻልና ሥራን በአግባቡ አለማከናወን ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በአጋጣሚ በትልቅ መድረክ ላይ ስለተነሱ እንጂ፣ በአገልግሎት ፈላጊዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብባቸው ናቸው፡፡ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን ያለበት መዋቅሩን ከሙስና፣ እንዲሁም ተገቢ ካልሆኑ ድርጊቶች ማፅዳት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድ ዜጋ መብቱን በሕጋዊ መንገድ ለማስከበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቀላሉ የሚደናቀፈው፣ መንግሥት መዋቅር ውስጥ በመሸጉ በኔትወርክ በተደራጁ ሙሰኞች እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ ክፍተቶችን መጠቀምና ከሕግ በተቃራኒ የሆኑ ብልሹ አሠራሮችን ማስፈን በመለመዱ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች አሠራሮች በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መንገድ እንዳይመሩ እንቅፋቶች እንዲበዙ ይደረጋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት ከዘመኑ ጋር እኩል እንዲራመዱ የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ብቁ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ሊኖሩዋቸው ይገባል፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው ሥራቸውን ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ የተደራጀ ሌብነት፣ ሙስና፣ ሥራን ማጓተት፣ የአገልጋይነት ስሜት ማጣት፣ ግድየለሽነትና የመሳሰሉ ብልሹ አሠራሮች የሚወገዱት ተቋማቱ ሲጠናከሩ ነው፡፡ በብሔር፣ በእምነት፣ በጥቅም ትስስርና በመሳሰሉት መረቦች በመጠላለፍ የሚባክነው የአገር ሀብት፣ ጊዜና ኢነርጂ በፍጥነት እንዲቆም ከተፈለገ ለመንግሥት ተቋማት መጠናከር ልዩ ትኩረት ይሰጥ፡፡ ተቋማቱ ሲጠናከሩ ሕግ መጣስ፣ በዘልማድ መሥራትና ተገልጋዮችን ማማረር ይቆማሉ፡፡ በእዚህ መሠረት ሥራን ማከናወን ሲቻል አመራሮችም ሆኑ ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ፡፡ ዘመኑ በሚፈልገው ቁመና ላይ ተገኝተው ብርቱ ተወዳዳሪ መሆን አያቅታቸውም፡፡ ባሉበት የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ለአገር ፋይዳ ስለማይኖራቸው፣ ተቋማቱና አመራሩ እንዲናበቡ ይደረግ!