ማሰቃየትና ኢ ሰብዓዊ አያያዝ እንዲሁም የዘፈቀደ እስር ተባብሶ ቀጥሏል

መብታቸውን የሚጠይቁ ግለሰቦች ለተደጋጋሚና ረጅም እስር ተዳርገዋል- የኢሰመኮ ብሔራዊ ምርመራ 

👉🏿 ማሰቃየትና ኢ ሰብዓዊ አያያዝ እንዲሁም የዘፈቀደ እስር ከፍተኛ ነበር

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአምስት ዓመታት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና የቀድሞ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ያካሄደውን የዜጎች ነጻነት የተመለከተ ብሔራዊ ምርመራ ይፋ አደረገ።

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ማሠቃየት እና ኢ-ሰበአዊ አያያዝ ሲል የጠቀሳቸው ደብዛን አጥፍቶ ማሰርን፣ በግዳጅ መሰወር፣ በእስር ቤቶች ውስጥ ክብርን ያልጠበቁ አካላዊ ፍተሻዎች፣ በቂ ምግብና ውሃ በሌላቸው፣ በተጨናነቁ፣ የንፅሕና እና የሕክምና አገልግሎት በሌላቸው እስር ቤቶች ማሰር አንዱ ግኝት ነው።

መብታቸውን የሚጠይቁ ግለሰቦችን ከድርጊቶቻቸው ለማስቆም በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜ አስሮ ማቆየት፣ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰር፣ የተጠርጣሪ ቤተሰብ አባላትን በምትክ ማሰር፣ በአደራ እስረኛነት ሰበብ ፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ለረዥም ጊዜ ማረሚያ ቤት ማቆየት፣ ፍርድ ቤት የሰጠውን የዋስትና መብት በመጣስ ማሰርን እንዲሁም መንግሥትን በፍትሐብሔር ጉዳዮች የከሰሱ ግለሰቦችን ማሰርን የመሰሉ የዘፈቀደ እስርም በክልሎቹ ተፈጽመዋል።

ከኮሚሽኑ ሪፖርት እንዳመለከተው የሕግ አማካሪ ጋር መገናኘትን መከለከል፣ የቤተሰብ ጉብኝት መከልከል፣ ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት፣ የመተዳደሪያ ገቢ ማጣት፣ ስለ ሰብዓዊ መብቶች በቂ ግንዛቤ አለመኖር እና ለጥሰቶቹ መፍትሔ እንዲሁም ማካካሻ ስርዓት አለመኖሩ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው በብሄራዊ ምርመራው ታውቋል።

በምርመራ ሪፖርቱ መሰረት “የሰብአዊ መብቶች ጥሰቱ የተፈጸመው በሚሊሻ አባሎች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የመደበኛ ፖሊስ አባላት፣ በቀድሞው የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት እና የመንግሥት ኃላፊዎች ነው”።

ኢሰመኮ ከሚያዝያ 2010 እስከ ሚያዝያ 2015 ድረስ ባደረገው ምርመራ የተገኙት “አንዳንድ” ጥሰቶች ተቋማዊ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን “በብዙ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የመፈጸም አዝማሚያን ያሳያሉ” ተብሏል።

በግኝቶቹ መሰረት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ የፌደራል እና የክልል መንግስታት የተሟላ የወንጀል ምርመራ እንዲያደርጉ እና ለተጎጂዎች ካሳ የሚሰጥበት ስርዓት እንዲያዘጋጁ መክሯል።

በተጨማሪም የፖሊስ አባላት ምትክ እስርም ሆነ መሰል ሕገ ወጥ እስሮችን ማቆምና በሚፈጽሙ አባላት ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት ተብሏል።

በአጠቃላይም ለጸጥታ እና የፍትሕ አካላት አስፈላጊው የመብቶችና የእስረኛ አያያዝ ግንዛቤ መስጠት፣ በማረሚያ ቤቶች ተከታታይ ክትትል ማድረግ እና የግለሰቦችን መብት ማክበር እንደሚገባ ኮሚሽኑ አጽንዖት ሰጥቷል።