በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ አለመረጋጋት ተፈጥሯል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ አለመረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በዚህም በሰው ሕይዎትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በደረሰው ጉዳት የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ሐዘን ጽሕፈት ቤቱ ገልጧል፡፡ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አሰማኸኝ አስረስ በደምቢያ ወረዳ እየተስተዋለ ባለው አለመረጋጋት በሰው ሕይዎትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል መንግሥት ማውገዙን ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ ሁለቱንም ሕዝቦች የማይወክል መሆኑ በተጨባጭ ማሥረጃ መረጋገጡንም ነው ያስታወቁት፡፡ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል የተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውንና የእሥር ማዘዣ የወጣባቸው እንዳሉም አቶ አሰማኸኝ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ መረጃ ግጭቱ ዳግም ያገረሸበት ምክንያት አካባቢውን ለማረጋጋት ተሰማርቶ የነበረው 24ኛ ክፍለ ጦር ወጥቶ 33ኛ ክፍለ ጦር ለግዳጅ ሊገባ እያለ ጥር 24/2011 ዓ.ም መንግሥት ‹‹የተደራጁ ቡድኖች›› ያላቸው አካላት በጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ነው፡፡

(አብመድ)