አየር መንገዱን አደራ! ( ኤሊያስ መሰረት )

አየር መንገዱን አደራ!( ኤሊያስ መሰረት )

ሀገራችንን ከአትሌቲክስ እና ከታዋቂው ቡናችን እኩል በአለም ደረጃ የሚያስጠራ እና የሚያስተዋውቅ አየር መንገድ አለን።

ተደጋግሞ እንደሚነሳው አየር መንገዱ በአፄው ስርዐት እና በደርግ ጭምር እምብዛም የፖለቲካ ጣልቃ-ገብነት ሳይኖርበት በአፍሪካ ቀዳሚው፣ በአለምም አሉ ከሚባሉ አየር መንገዶች ተርታ ተሰልፏል።

ይህ የሀገር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት የሆነ አየር መንገድን በሼር ለመሸጥ የዛሬ አምስት አመት ሀሳቡ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ትኩሩቱ ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ዞሮ የአየር መንገዱ ጉዳይ የቀረ መስሎ ነበር።

ይሁንና ከሰሞኑ፣ በተለይ በትናንትናው እለት እንደተዘገበው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ወደብ በረዥም ግዜ ሊዝ ለመከራየት በፈረመችው የመግባብያ ሰነድ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሼር ለሶማሌላንድ እንደሚሰጥ ታውቋል።

ጥያቄዬ እዚህ ጋር ነው።

እስከሚገባኝ የአየር መንገድ ቢዝነስ ለየት ያለ መልክ ያለው ነው። እንደ አውሮፕላን አምራቾች፣ አውሮፕላን አከራዮች እና ገንዘብ አበዳሪዎች ያሉ በርካታ አጋሮች እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በትኩረት ይከታተላሉ፣ ችግር ያለ ሲመስላቸው ያፈገፍጋሉ። በርካታ በሊዝ የገቡ አውሮፕላኖች አሉን፣ አውሮፕላኖች የሚገዙት ደግሞ በብድር ነው።

ስለዚህ አይደለም የበርካታ ቢልዮን ዶላር interest ያላቸው እነዚህ ተቋማት የአቪዬሽን ተንታኞች እና መንገደኞች እንኳን ይህን ይመለከታሉ።

በተጨማሪም አየር መንገዱን የከረረ ጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ ያለበት ጉዳይ ውስጥ መጣድ ለአድማ፣ እንዲሁም አያድርስና ለጥቃት ጭምር ሊያጋልጠው ይችላል። አንዳንድ የሶማልያ ብሎገሮች ካሁኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አትብረሩ፣ ወደ ሀገራችን አይብረር… ወዘተ ንትርክ ጀምረዋል።

ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ያስነሳው የሶማልያ ሉአላዊነት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ወደብ ማግኘት በራሱ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ነገር ግን አየር መንገድ ያለበትን sensitive ገበያ ባማከለ መልኩ እሱን ከሼር ከማቅረብ ቀድሞውን የሼር ሽያጭ ንግግር በጀመሩ ተቋማት ማስቀጠሉ የተሻለ ይመስለኛል።

ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበት እዚህ የደረሰን አየር መንገድ አደራ!

መልካም ምሽት! ( ኤሊያስ መሰረት )