ይህን ጦርነት በቀዳሚነት መቃወም ያለበት የኦሮሞ ሕዝብ ነው!

ይህን ጦርነት በቀዳሚነት መቃወም ያለበት የኦሮሞ ሕዝብ ነው!

1) የኦሮሚያ ብልፅግና በሀሰት አማራ ኦሮሞን ሊያጠፋ ንቅናቄ የጀመረ አስመስሎ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ያወጀው ጦርነት ነው። የሕዝብ ጦርነት ለማድረግ ቅስቀሳዎች አሉ። በስሜ አይሆንም መባል አለበት። ከዚህም ከዛም ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ አስተያየቶች ተለምደዋል። እነዚህን ያልተገቡ አስተያየቶች በጋራ ማስቆም ነው። በዋነኛነት ግን እነዚህ አልፎ አልፎ የምናያቸው አሉታዊ በሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ አስተያየቶች ገዥዎቹ ለራሳቸው ስልጣን የሚጠቀሙባቸው እንጅ የሕዝብ ዋነኛ መገለጫዎች አይደሉም። ስለሆነም ሰበብ ሳያስፈልግ ጦርነቱ የእኛ አይደለም ማለት ያለበት የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል የሚለው፣ ሰፋ ሲልም ሕዝቡ ነው።

2) የአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመበት ያለውን በደል ከኦሮሞ ሕዝብ የተሻለ ሊገነዘብ የሚችል የለም። ኦሮሚያ ውስጥ በገዥዎቹ መዋቅር ጭምር የተፈፀመውን ያውቃል። “ተዋቸው” ሲል “ምን አገባህ አንተ ኦሮሞ ነህ!” ተብሎ ተወቅሶ ጭምር በአይኑም ያየው በደል ነው። የአማራ ሕዝብ ብቻውን መጮህ አልነበረበትም። ሲበደል ያየው የኦሮሞ ሕዝብም አብሮት መጮህ ነበረበት። ኦሮሞ በደል ሲደርስበት በአፈና ወቅት በአደባባይ ለኦሮሞ ሕዝብ አጋር የሆነው የአማራ ሕዝብ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የአማራን ሕዝብ ትግል በይፋ ባይደግፍ እንኳ ከበደል የመጣ መሆኑን በየቀየው ከተፈፀመው ዘር ፍጅት ያውቀዋልና የፍትሕ ጥያቄ መሆኑን አውቆ በእኛ ስም የጀመራችሁትን ጦርነት አቁሙ ማለት አለበት።

3) የኦሮሞ ሕዝብ በወርድና ቁመቴ ልክ ውክልና ያስፈልገኛል፣ ስልጣን ይገባኛል ሲል እንደነበረው የአማራ ሕዝብ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የውክልና ጥያቄ አለው። አሁን አደባባይ ላይ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ጥያቄዎች ስላልተመለሱ የመጣ ነው። ገዥዎቹ ይህን ጥያቄ የሃሰት ስም ሰጥተው እንደፍቃለን ሲሉ በስማችን የሕዝብ ጥያቄ ለማፈን አትጣሩ ማለት አለበት።

4) ይህ ጦርነት አገር አፍራሽ ጦርነት ነው። ሰራዊቱን ያለ ቦታና ስልጠናው እንደ ፖሊስ በየቀበሌ አስገብተው እያስመቱት ነው። ከሕዝብ ጋር ደም እያቃቡት ነው። ጭካኔ እየፈፀሙ ነው። በኦሮሞ ሕዝብ ስም ስልጣን በተያዘበት ወቅት አገር መፍረስ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው።

5) አብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን መነጠል የሚፈልግም ካለ ነገ ጎረቤቱ የአማራ ሕዝብ ነው። ዛሬ ባልተገባ መልኩ ለነገ ቁርሾ ማትለፍ ተገቢ አይደለም። ስለሆነም በስሜ ወንጀል፣ በስሜ ጭካኔ፣ በስሜ ትርክት፣ በስሜ ጥላቻ አታስመዝግቡብኝ ብሎ ቀድሞ መቃወም አለበት።

6) የኦሮሞ ሕዝብም ከዚህ በደል ነፃ አይሆንም። ሌሎችን አፍኖ ወደ ኦሮሞ ሕዝብ ይመለሳል። ለስልጣናቸው ስላሰቡ እንጅ ለኦሮሞ ሕዝብ ቢያስቡ ይህን አያደርጉም ነበር። በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ኦሮሞው ላይም በደል እንደሚፈፀም ይታወቃል።በደሉ የጋራ ነው። ይቁም ተብሎ አሁኑኑ መጠየቅ ያለበት ከኦሮሞ ኃይል ነው።

ይህ ሲሆን አማራውም ከሕዝብ ስነ ልቦና ባፈነገጠ መልኩ ያልተገባ መልዕክት የሚያስተላልፉትንና ሕዝብ ተናገሩልኝ ሳይላቸው በተሳሳተ መልኩ እንዲታይ የሚያደርጉትን የእኛ ወገን አይደላችሁም ብሎ ማውገዝ ግድ ይለዋል።