በኢትዮጵያ አስራ አንድ ከተሞች 88,960 ጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉ መሆናቸው በጥናት ሲረጋገጥ 50,000 ያህሉ በዋና ከተማዋ መዲና ጎዳናዎች ይኖራሉ።

[addtoany]

DW – በኢትዮጵያ አስራ አንድ ከተሞች 88,960 ጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉ መሆናቸው በጥናት ሲረጋገጥ 50,000 ያህሉ በዋና ከተማዋ መዲና ጎዳናዎች ይኖራሉ።

የጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሄ ያልተገኘለት ችግር ሆኗል። ሥራዎች ቢሰሩም ዛሬም ስር ነቀል እልባት ላይ አልተደረሰም እየተባለ ነው። በኢትዮጵያ አስራ አንድ ከተሞች 88,960 ጎዳና ተዳዳሪዎች ያሉ መሆናቸው በጥናት ሲረጋገጥ 50,000 ያህሉ በዋና ከተማዋ መዲና ጎዳናዎች ይኖራሉ።

ሜክሲኮ ኮሜርስ፣ መስቀል አደባባይ፣ ፒያሳ አካባቢ ከሌላው በተለየ በጎዳና የእለት ክስተት ይመለከታሉ – መኪኖች የትራፊክ መብራት በያዛቸው ዘንድ ልመና አልያም መስታወት ጠርገው ብር የሚጠይቁ የጎዳና ልጆችን። እነዚህን አዳጊዎች ከጎዳና ህይወት ለማውጣት ስራዎች ቢሰሩም ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ ሆኖብናል ሲሉ በስራው የተሰማሩ አካላት ይናገራሉ። ወደ ጎዳና ህይወት መልሶ መግባታቸው “ችግሩ ከስሩ ባለመቀረፉ ምክንያት ነው”ይላሉ።

ለጎዳና ህይወት ተጋላጭ ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍል ወጣቱ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ አቶ እንደሻው አበራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግር ተረጂዎች መልሶ ማቋቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ይገልጻሉ። “ለጎዳና ህይወት ተጋላጭ የሆኑት የህብረተሰብ ክፍል አምራቹ ክፍል በተለይም እድሜያቸው ከ15 እስk 29 ክልል ያሉት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። በሀገሪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች 88,960 ንሮአቸውን በጎዳና ሲያደርጉ 50,000 ያህሉ በአዲስ አበባ ጎዳና ይኖራሉ።”

አቶ እንደሻው ወደ ቤተሰብ የመመለሱ ስራ የተሰራ ቢሆንም ውጤታማ ግን አልሆነም ብለዋል። ለዚህም በዋናነት የክትትል ስራ አለመሰራቱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። “ወደ ቤተሰብ የመመለሱ ስራ ከዚህ በፊት በመንስግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ተሰርቷል። ውጤታማ ሆኖ ግን አልተገኘም።” የስነ ልቦና ስራ መሰራት አለበት የሚሉት አቶ እንደሻው ከልጆቹ በበለጠ የችግሩ ምንጭ ላይ ቤተሰብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስረግጣሉ።

“ከዚህ በፊት ከነበረው በተጠናከረ ስነ ልቦናቸው ላይ ይሰራል። የችግሩ ምንጭ በሆነው ቤተሰብ ላይ መሰራት መቻል አለበት።” ሪትራክ ኢትዮጵያ ለችግር የተጋለጡ ህጻናትና በጎዳና የሚኖሩት ህብረተሰብን የሚረዳ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በዋናነት በጎዳና የሚኖሩትን ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለስን ስራን እንደሚሰራ አቶ ደረጀ ዘለቀ የሪትራክ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ይገልጻሉ። ድርጅታቸው ለችግሩ ትኩረት ቢሰጥም አሁንም ግን ሊቃለል አልቻለም ይላሉ። “በዋነኛነት ወደቤተሰቦቻቸው የመመለስ ስራ ነው የምንሰራው። ካልሆነ የሙያ ስልጠና ነው የምንሰጠው።

ቤተሰቦቻቸው ጋር ተመልሶ ለመኖር አንዱ ተግዳሮቱ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከርን ነው።”  አቶ ደረጀ በጎዳና ለሚኖሩ ልጆች የስነ ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ የትብብር ስራም መሰራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።  ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጉዳዩ ተሳታፊ ሊሆን ይገባልም ሲሉ ያሳስባሉ።