ግንባታዎችን በውላቸው መሰረት ያላጠናቀቁ የሥራ ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጦ ከስራ ውጪ ሊሆኑ ነው ተባለ

ግንባታዎችን በውላቸው መሰረት ያላጠናቀቁ የሥራ ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጦ በቀጣይም በማንኛውም የከተማዋ ግንባታዎች ላይ እንዳይሳተፉ ይደረጋል

በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በውላቸው መሰረት ያላጠናቀቁ የሥራ ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጦ በማንኛውም የከተማዋ ግንባታ እንዳይሳተፉ ሊደረግ መሆኑን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ገለፁ።

የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ፕሮጀክቶቹን ከሚያሰሩት የከተማዋ መንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ የፕሮጀክቶቹን አጠቃላይ አፈፃፀም ለከተማዋ የኮንስትራክሽን ቢሮ እንዲያቀርብ ምክትል ከንቲባው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክቶችን ከሚሰሩ ሥራ ተቋራጮች ጋር በግንባታ መጓተት ዙሪያ በተጠራው ስብሰባ የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ብዙዎቹ በውላቸው መሰረት እየሄዱ አይደለም ተብሏል።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ በመንግስት በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች መጓተትን በተመለከተ ጉዳዩ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረና መፍትሄ ያላገኘ መሆኑን ገልጸው በገቡት ውል መሰረት ግንባታን የማያከናውኑ የሥራ ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጦ በቀጣይም በማንኛውም የከተማዋ ግንባታዎች ላይ እንዳይሳተፉ ይደረጋል ብለዋል።