ሜጀር ጄኔራል ክንፈን ጨምሮ ስምንት ተከሳሾች ከ319 ሚሊየን ብር በላይ በማባከን ክስ ተመሰረተባቸው

ሜጀር ጄኔራል ክንፈን ጨምሮ ስምንት ተከሳሾች ከ319 ሚሊየን ብር በላይ በማባከን ክስ ተመሰረተባቸው

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በስምንት ግለሰቦች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ከ319 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ክስ መሰረተ፡፡

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15 ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ፣ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ፣ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ፣ አቶ ቸርነት ዳና፣ እሌኒ ብርሃን እና ሮመዳን ሙሳ ናቸው ፡፡

ስምንቱ ተከሳሾች ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ሰባት ክሶች ቀርቦባቸዋል፡፡

በችሎቱ አራተኛ፣አምስተኛ እና ሰባተኛ ተከሳሾች በሌሉበት ነው የክስ ዝርዝራቸው የተነበበው፡፡

በክስ ሰነዱ ላይ እንደተመላከተው በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተር እና የትራክተር ተቀጽላዎች ግዥ ያለግልፅ ጨረታ፣ ያለግዥ ፍላጎት እና ለሁሉም አቅራቢዎች እኩል እድል ባልሰጠ መልኩ ተፈፅሟል፡፡

በዚህም መንግስት ከገቢያ ውድድር ሊያገኝ የሚችለውን የጥራት፣ የዋጋና የአቅርቦት ጥቅም ጎድተዋል ያለው ከሳሽ አቃቢ ህግ ይህንም ለማስረዳት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰባሰቡን በክስ ዝርዝሩ አያይዞ አቀርቧል፡፡

ተከሳሾች የክስ መዝገቡ በችሎቱ ውስጥ ስለደረሳቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት መቃዋሚያቸውን ለማቅረብ ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀዋል፡፡

አቃቢ ህግ በእንግሎዘኛ ቋንቋ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በአማረኛ ተተርጉመው በ10 ቀናት ውስጥ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም ለጥር 17 ቀን 2011 አመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡