የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የክልል ልዩ ኃይሎች የቡድን መሣርያዎችን ለመከላከያ እንዲያስረክቡ እና ወደ መደበኛ ፖሊስና ወደ ማረሚያ ቤት ፖሊስ እንዲቀየሩ መወሰኑ ተሰምቷል። ይህ ውሳኔ ጊዜውን ያልጠበቀ፤ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው፤ በተለይም ጥቃት ያንዣበበበትን ሕዝብ ለማስመታት ያለመ አደገኛ ወሳኔ ነው።
1) ከምንም በፊት በውሳኔው ላይ የተሳተፈው አመራር በሙሉ በቀጣይ ለሚፈጠር አገራዊ ትርምስ እና የሕዝብ ጥቃት ተጠያቂ መሆኑ መታወቅ አለበት። በተለይ በማንነቱ ተለይቶ እየተጠቃ ያለው፤ በሐሰት ትርክት የተደራጁ ታጣቂዎች በየአቅጣጫው እያጠቁት የሚገኘው አማራን ወክያለሁ ብሎ በውሳኔው የተሳተፈ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አመራር ለዚህ ታሪካዊ ስህተት ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል።
2) ውሳኔው የተወሰነው በሽብተኝነት ተፈርጀው የነበሩ ታጣቂዎች መሣርያ ሳያወርዱ፤ ይልቁንም እንደ ትህነግ ያሉት የጥፋት ኃይሎች ተጨማሪ ሠራዊት እያሰለጠኑ እና በየአካባቢው እነዚህ ታጣቂዎች ጥቃት እየፈፀሙ ባሉበት ወቅት መሆኑ ሕዝብን ያለ ፀጥታ ኃይል ከለላ ለጥቃት የሚያጋልጥ እጅግ አደገኛ ውሳኔ ነው። ለአገር ህልውናና ዘላቂ ሰላም ቢታሰብ ኖሮ ከማንም በፊት ትጥቅ መፍታት የሚገባቸው በአገርና በሕዝብ ላይ መጠነ-ሰፊ ጥፋት የፈፀሙትና እየፈፀሙ ያሉት ትህነግና ኦነግ-ሸኔ ነበሩ፡፡ ሆኖም እየሆነ ያለው ከዚህ ተቃራኒ በመሆኑ እንዳይኖሩ የተፈለጉት አገርና ሕዝብን የታደጉት እንደ አማራ ልዩ ኃይል ያሉት ናቸው፡፡ ውሳኔውን ፍፁም ኃላፊነት የጎደለውና አደገኛ የሚያደርገው ይህ ነው፡፡
3) በሰላም ስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የትግራይ አካባቢዎችን ይቆጣጠራል ሲባል ጥሎ በወጣበት፣ ትህነግ ትጥቅ እንዳይፈታ በተደረገበት፣ ኦነግ-ሸኔ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ እየገባ ያልተቋረጠ ጥቃት እየፈፀመ ባለበት እና የፌደራል ፀጥታ ኃይል ለሕዝብ ባልደረሰበት ሁኔታ የየአካባቢውን ሕዝብ ለጊዜው የሚጠብቁ ልዩ ኃይሎች ላይ የሚወሰነው ውሳኔ ለአጥቂዎቹ አቅም የሚሰጥ መሆኑ እሙን ነው። እንደ ትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ ካሉት በተጨማሪ የጎረቤት አገር ኃይልን ጥቃት እየመከቱ ያሉ ልዩ ኃይሎች እንዳሉ እየታወቀ እነዚህ ስጋቶች ባልተቀረፉበት በአንድ ፓርቲ ውሳኔ የሚደረገው ትጥቅ ማስፈታትና ልዩ ኃይሎችን መበተን አገርንም ጭምር ለአደጋ ያጋለጠ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
4) ትክክል ሆነም አልሆነም የክልል መንግሥታት የየክልሎቹን ፀጥታ ኃይሎች እንዲያዋቅሩ በሕግ የተቀመጠና ሲሠራበት የቆየ ጉዳይ ነው። ይህ ሕግና አሠራር መሻር ካለበትም ሥርዓቱን ጠበቅ መሻር ይኖርበታል፡፡ መታወቅ ያለበት፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠበቅበትን የዜጎችን ሕይወት የመጠበቅ ኃላፊነት መወጣት ባለመቻሉ ምክንያት የየክልሉ ሕዝብም የየአካባቢውን ልዩ ኃይል ከጥቃት ያድነኛል ብሎ ያምናል። ስለሆነም ሕገ-መንግሥቱ ሳይሻሻል፣ ሕዝብ ጋር ውይይት ሳይደረግ፣ የክልል ምክር ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሳይወያዩበት፣ መሰል ጉዳዮችን ይፈታል ተብሎ የሚታሰበው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሳያጠና በአንድ ያውም ተደጋጋሚ ስህተት በፈፀመ፣ ታማኝነቱን ባጣ እና የራሱን ችግር ለመፍታት በተቸገረ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የሚደረገው ውሳኔ ቅቡልነት የሌለው፣ ለተቃውሞና ትርምስ የሚዳርግ፣ ካለው ሕግና አሠራር አንፃር ሕገ-ወጥ መሆኑ መታወቅ አለበት።
5) ይህን ውሳኔ የወሰነው ብልጽግና ፓርቲ እርስ በእርሱ በሥልጣን ሽኩቻና መፈንቅለ መንግሥት በሚካሰስበት ወቅት የተወሰነው ይህ ውሳኔ እስካሁን ካለው አካሄድ ጠባብ ቡድናዊ ጥቅምና ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ሌሎችን ለማጥቃት እንደሆነ የማያሳዩ መረጃዎች አሉ። ባለው የሥልጣን መዛነፍና አፈፃፀም በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ አፈፃፀም እንደማይኖረው የሚታመን ከመሆኑም በላይ በተለይ እንደ አማራና አፋር ያሉ ክልሎች ላይ ሆን ተብሎ ጥቃት ለማስፈፀም የተደረገ ደባ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህ ውሳኔ የአማራና አፋር ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ትጥቅ መፍታት ለነበረበት ትህነግ ታጣቂ እድል ሰጥቶ ሁለቱ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ጦርነት የሚያሳውጅ ውሳኔ ነው።
6) የፌደራል መንግሥትም ሆነ መከላከያ ሠራዊት ኦነግ-ሸኔ ጋምቤላ ከተማ ሲደርስ ሕዝብን አልታደጉም። አጣዬ ስትቃጠል አልደረሱም። ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ገብቶ አካባቢውን ሲያተራምስ የደረሰ የለም፡፡ በየክልሉ ኦነግ-ሸኔ ትርምስ ሲፈጥር ፀጥታ አላስከበሩም። ይህን አቅም ባላዳበሩበትና ፍላጎት ባጡበት ወቅት እነዚህ በሽብር የተካኑ ቡድኖች የትም ሄደው ጥቃት እንዲፈፅሙ እድል የሚያመቻች ውሳኔ ነው። የአንዳንድ ክልሎች ፀጥታ አካላት አሁንም ስልጠና እየወሰዱ፣ ለመከላከያ ሰራዊት መሳርያ እያዋሱ ባሉበት አተገባበሩ እኩል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። በተለይ ጥቃት ለመፈፀም እየጣረ የሚገኘው ትህነግ ትጥቅ እንዳይፈታ በተደረገበትና ለቀጣይ ጥቃት በተሰለፈበት የአማራና የአፋር ሕዝብን እንዲጠቃ የሚያመቻች፣ በተለየ ሁኔታ ትህነግ ሌት ተቀን ለጥቃት እቅድ የሚያወጣባቸውን የራያ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እና አበርገሌ ንጹሐን ላይ ሌላ ዙር በቀልና ዘር ፍጅት እንዲፈፀም የሚያመቻች ነው። ውሳኔው አገሪቱን ወደ ሰላም ሳይሆን ወደ እልቂትና ትርምስ የሚስገባ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
7) አደጋውን የሚረዱት የልዩ ኃይል አዛዦች፣ አባላትና ሕዝብ በሚኖረው መከፋት እና እርስ በእርስ ግጭት አገር ከየአቅጣጫው ጦርነት ውስጥ እንድትገባ የታቀደበት አደገኛ ውሳኔ በመሆኑ በአስቸኳይ ተሽሮ ሒደቶችንና ስጋቶችን ባገናዘበ መልኩ መፈፀም ይኖርበታል። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ሕዝብ የዘር ፍጅት የታወጀበት መሆኑን እና የሚከላከልለት አካል እንዳይኖር የተደረገበት መሆኑን አምኖ ውሳኔውን በአደባባይ መቃወምና ማስቀየር ይኖርበታል!