የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተገደሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የነቀምቴ ከተማ የገዢው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገደሉ።

የነቀምቴ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ቦኮንጃ በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት የተገደሉት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም. ነው።

ግድያውን በተመለከተ የከተማ አስተዳዳሩ “ለሥራ ከቤታቸው ሲወጡ ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ” በማለት በፌስቡክ ገጹ ላይ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።

በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የ33 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ደሳለኝ ላይ ግድያው የተፈጸመው ከቤታቸው ደጃፍ ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ግድያውን ተከትሎ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የተሰማቸውን ሐዘን መግለጻቸውን ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ፍቃዱ በፓርቲያቸው ከፍተኛ ኃላፊ ላይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ በ“ታጠቀ አካል” መፈጸሙን አመልክተዋል።

ቢቢሲ በግድያው ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ከነቀምቴ ከተማ አስተዳደር እና ከፀጥታ አካላት ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ በምትገኘው ነቀምቴ ከተማዋ ከዚህ በፊትም የመንግሥት የፀጥታ እና የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢ አስተዳዳሪዎችን ኢላማ ባደረጉ ተመሳሳይ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ለእነዚህ ግድያዎች መንግሥት ሸኔ የሚለው እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን የከተማ ክንፍ የሆነው “አባ ቶርቤ” የሚባለውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቢያስተባብልም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነቀምቴን ጨምሮ በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ ዞኖች እና ከተሞች ውስጥ ከሚፈጸሙ ግድያዎች እና ጥቃቶች ጋር በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል።

ምንም እንኳን አማጺው ኃይል የእንቅስቃሴ አድማሱን ባለፉት በርካታ ወራት እየሰፋ መምጣቱ ቢነገርም እንዲህ ያለው ግድያ ስለመፈጸሙ በቅርቡ ተስምቶ አያውቅም ነበር።

ይህ አሁን የተፈጸመው የኃላፊው ግድያ የተሰማው መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ ግጭት በንግግር ለመፍታት ጥረቶችን እያደረገ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተገለጸ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

የነቀምቴ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ ደሳለኝ ቦኮንጃ ላይ አሁን ስለተፈጸመው ግድያ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።

አቶ ደሳለኝ በፓርቲው ውስጥ ከያዙት ከፍተኛ ኃላፊነት ቀደም ብሎ በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።

ግድያውን አስመለክቶ የከተማው አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አቶ ደሳለኝ “የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት እና በተቆርቋሪነት. . . ያለምንም ፍርሐት” ሕዝቡን ሲያገለግሉ ነበሩ ብሏል።

ግድያው በማን እና እንዴት ስለመፈጸሙ የአካባቢው ፖሊስ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፣ የከተማዋ አስተዳደር ግን ኃላፊው ከቤታቸው ሲወጡ በራቸው ላይ መገደላቸውን ገልጿል።

የኦሮሚያ ብልጽግና ጽህፈት ቤት በበኩሉ አቶ ደሳለኝ “ጠዋት ወደ ሥራ ለመሄድ በተነሱበት ጊዜ በታጠቀ ኃይል የጭካኔ ግድያ ተፈጽሞባቸው ሕይወታቸው አልፏል” ብሏል።

አቶ ፈቃዱ በሐዘን መግለጫው ላይ ግድያውን የፈጸሙ አካላትን በስም ባይገልጹም “ከአገሪቱ የለውጥ መንገድ በተጻራሪ የቆሙ አካላት” ብለዋቸዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ ከተሞች እና ዞኖች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ የአካባቢ አስተዳደር ባለሥልጣናት እና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ተገድለዋል።

ለእነዚህ ግድያዎችም መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት የተፈረጀው ሸኔ የሚለውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ ያደርጋል።

ቡድኑ ግን በየትኛውም ግድያ ውስጥ እጁ እንደሌለበት ሲያስተባብል ቆይቷል።