በደራ ራቾ አካባቢ የሸኔ ታጣቂዎች ያልተቋረጠ ጥቃት በማድረስ ላይ መሆናቸው ተሰማ

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ራቾ በሚባል አካባቢ የሸኔ ታጣቂዎች በንጹሃን ላይ ከቅዳሜ መጋቢት 16 ጀምሮ ጥቃት በማድረስ ላይ መሆናቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በጥቃቱ በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል ያሉት ምንጮች፣ ከ100 በላይ ሰዎች መታገታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

የራቾ አካባቢ በውስጡ አራት ቀበሌዎችን የያዘ ነው ያሉት ምንጮች በሀርቡ ድሬ፣ ሀሙማ ገንዶና ባቡ ድሬ ቀበሌዎች ላይ ጥቃቱ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ታጣቂዎቹ ከቀበሌው ነዋሪዎች መከላከል ይገጥመናል ብሎ በማሰብ በሆሮ ግንደ በርበሬ ቀበሌ ላይ ጥቃት አለማድረሳቸው ተሰምቷል፡፡

ቀበሌዎች በግብርና የሚተዳደሩና አምራች የሚባሉ ናቸው ያሉት ምንጮች፣ ከጥቃቱ የሚተርፉ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን ለዓመት የሚጠቀሙበት ምርት መውደሙን ተናግረዋል፡፡

ጥቃት በደረሰባቸው ቀበሌዎች ያሉ ነዋሪዎችን በስልክ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑንም በወረዳዋ ዋና ከተማ ጉንዶ መስቀል ያሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በሚገኘው ባቡ ድሬ ቀበሌ የፌደራል ፖሊስ ካምፕ ይገኛል ያሉት ምንጮች፣ እስካሁን ድረስ በታጣቂዎች ላይ እርምጃ አለመውሰዱን ገልጸዋል።

በዚሁ ቀበሌ በርካታ የሸኔ ታጣቂዎች እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን፣ በታጣዊዎች ላይ እርምጃ በሚወሰድበት መንገድ ዙሪያ የፌደራል ፖሊስ ዩኒፎርም በለበሱ የጸጥታ ኃይሎችና በወረዳው ሚሊሻዎች መካከል ግጭት መፈጠሩም ይታወሳል።

ምንም እንኳን ቤት ማቃጠሉ ቅዳሜ ዕለት የጀመረ ቢሆንም፣ ታጣቂዎቹ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማገት ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ ከጀመሩ በርካታ ጊዜያት መቆጠራቸውንም ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎች ላይ እርምጃ አለመውሰዳቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነም ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሌሎች ቀበሌ ሚሊሻዎች ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሄደው በታጣቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድም የወረዳው አስተዳደር ፍቃድ እንዳልሰጠና በሚሊሻዎች ላይ ሥም የማጥፋት ዘመቻ እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አዲስ ማለዳ የወረዳውን አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ወደ ወረዳው አስተዳደር የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አለባቸው ኃይለ ማርያም ተደጋጋሚ የሥልክ ሙከራዎችን ብታደርግም፣ መረጃዎችን አጠናቅሬ መልስ እሰጣለሁ በማለት ለቀናት በተደረጉ ተደጋጋሚ ጥረቶች መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

አዲስ ማለዳ