ታላቁ የአማራ ጉባዬ ፟፣ ብሶት ማሰሚያ ወይስ ለትግል ክተት የሚያውጅ ? #ግርማካሳ

ታላቅ የአማራ ማህበር ጉባዬ በዋሺንገትን ዲሲ ነገ ቅዳሜ ማርች 25 እና እሁድ ማርች 26 ይደረጋል፡፡ በዚህ ጉባዬ በርካታ የማውቃቸው ወገኖች ይሳተፋሉ፡፡ ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ያላችሁ ፣ በየቤታችሁ በአገራችሁ እየሆነ ባለው ነገር የታመማችሁ፣ በቤታችሁ ማልቀሳችሁን አቁማችሁ፣  ወደ ዚህ ስብሰባ ሄዱ፣ ከሌሎች ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር ለተግባራዊ ስራ ምከሩ፡፡  በዚህ አጋጣሚ ይህ ጉባዬ የተሳካ እንዲሆን ምኞቴን እየገለጽኩ ጉባዬው ትኩረት ቢሰጣቸው ጥሩ ነው የምላቸውን አንዳን ሃሳቦች  በአክብሮት ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ጉባዬው በተለይም ያሉትን ችግሮች በመተንተን ላይ ጊዜዉን ማጥፋት ያለበት አይመስለኝም፡፡፡ ከበቂ በላይ፣ ያለውን ችግር ሁሉም ሰው ያውቀዋል፡፡ ለቀባሪው አደረኡት ነው የሚሆነው፡፡ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡ የጉባዬው ተሳታፊዎች በአዲስ ድምጽ ሜዲያ ላይ ቀርበው ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ በግሌ በተለያም ያለፈውን በመተንተን ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች በማቅረብ ተሰባሳቢዉን ማሰልቸት ተገቢ አይደለም፡፡ በኔ እምነት ስብሰብው “ምን ተደረገ ? ምን ሆነ ?” በሚለው አጀንዳ ሳይሆን ፣ “ምን እናድርግ ?” በሚለው ላይ ነው 95% ጊዜውን ማጥፋት ያለበት ባይ ነኝ፡፡ ተግባራዊ የሆነ፣ የተጨበጠ፣ ህዝቡን የሚያንቀሳቀስ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ተላልፈው፣  አዘጋጆች በአዲስ ድምጽ ሜዲያ ያሉት፣ “ክተት” የሚለውን አባባል ልጠቅምና፣ በክተትና በቁርጠኝነት እንቅስቃሴ የሚጀመርበትን ሁኔታ በጉባዬውይመቻቻል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡
ሌላው ደግሞ ይህ የአማራ ስብስብ፣ አማራ ካልሆኑት ጋር አብሮ የመስራት ፕሮቶኮል ቢዘረጋ ጥሩ ነው፡፡ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ወዘተ እየተባለ፣ አማራ ክልል ላይ ብቻ ያተኮረ፣ በተለይም የአዲስ አበባን ህዝብ ያላቀፈ እንቅስቃሴ የትም አይደርስም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ደግሞ ምን አይነት አመለካከት እንዳለው የሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የአማራ ስብስብ፣ በአማራነት የሚሰራው እንደተጠበቀ፣ ከሌሎችም ጋር በጋራ የሚሰራበትን ሁኔታ በቶሎ ማመቻቸት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ኦህዴዶች ወዳጆች ለማፍራት፣ ለማብዛት አይደለም እንዴ ህወሃትን ከሽብተኛ ሊስት ውስጥ የሰረዘሩት ?  ሌሎች ወዳጆች፣ አጋሮች ሲያበዙ  የአማራ ኃይሎችም እንደውምየበለጠ ማድረግ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡
ይሄን ብዬ ስለ ጉባዬውና ስለ አማራ ድርጅቶች ጠቅላል ያለ አስተያየት እንዳቀርብ ፍቀዱልኝ፡፡
ይህ ጉባዬ የአማራዎች ጉባዬ ቢሆንም፣ አንድ በትልቁ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያን ለማዳን የተጠራ ጉባዬ ነው፡፡
የኦሮሞ ብሂረተኞች ከዚህ በፊት በአትላንታ፣ በለንደን በመሳሰሉት የተለያዩ የኦሮሞዎች ኮንፈራንሶች አድርገው ነበር፡፡ ምንድን ነበር ሲሉ የነበሩት ? “ታላቋን ኦሮሚያ ለመገንባት ኢትዮጵያ መበተን አለባት”አልነበረም እንዴ ሲሉ የነበሩት ?
የኦሮሞ ብህረተኞች አጀንዳቸው የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ ሳይሆን ኢትዮጵያን መበትን ነው፡፡ አጀንዳቸው ኦሮሞ ከሌላው ኢትዮያዊ ወንድሙ ጋር ተፋቅሮ፣ ተዋዶ ፣ ተስማምቶና ተሳስሮ፣ በሰላምና በእኩልነት በአንድነት እንዲኖር ሳይሆን፣ ኦሮሞ ከሌላው ተለይቶ፣ የራሱን፣ ከኢትዮጵያዊነት የጸዳ ማንነት አዳብሮ፣ ኦሮሞ ብቻዉን ልዩ ተጠቃሚ ሆኖ፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው አይነት አባ ገዳዊ ጭፍለቃን ለመፈጸም ነው ፡፡ የኦሮሞ ብሄረተኖች ይኽው አራት ኪሎን ተቆጣጥረው እየፈጸሙት ያለውን የምናውቀው ጉዳይ ነ፡ው፡
የአማራ ድርጅቶችና ስብስቦች፣ እንዲሁም ፣ ይህ የተጠራው የአማራ ጉባዬ ግን በዋናነት አጀንዳው፡
1ኛ ሰብአዊነት ነው፡፡ በአማራው ማህበረሰብ ላይ በኦሮሞ የኦህዴድ እና ኦነግ ኃይሎች እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጻድት ወንጀሎችን ማጋለጥ፣ መታገልና ማስቆም ነው፡፡ ከ10 ሺህ በላይ በማንነታቸው በኦሮሞ ክልል በቤኔንሻጉል የተገደሉ አማራዎች ፍትህ እንዲያገኙ ፣ በማንነታቸው የተፈናቀሉ ሚሊዮኖች ወደ ቅያቸው እንዲመለሱና የደህንነት ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡
2ኛ የአማራውን ህልውናን ማስጠበቅ ነው፡፡ አማራው በሁሉም አገሪቷ በሰላም፣ በፍቅር ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ጋር በሰላም መኖር እንዲችል ማድረግ ነው፡፡
3ኛ እኩልነትንና ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ አማራውን የበላይ ለማድረግ ሳይሆን፣ አማራው ከሌላው ጋር በሰላም፣ በፍቅር ፣ በእኩልነት እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ አማራው ለምሳሌ አዲስ አበባ የኔ ናት አይልም፣ የኦሮሞ ድርጅቶች ፊንፊኔ ኬኛ እንደሚሉት፡፡
4ኛ የዘር ፖለቲካ፣ የዘር ሕግ መንግስት፣ የዘር አወቃቅር ተቀይሮ፣ በዜግነትላይ የተመሰረተ ስርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ ነው፡፡ የአማራ ድርጅቶች ይህ አይነት ስርዓት ቢዘረጋ፣ ደስ ብሏቸው በአማራ ስም እያደረጉት ያለውን መሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያዊነት ለመቀየር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ “አማራ፣ አማራ” መባል የተጀመረው እኮ፣ አማራው ብቻዉን ኢትዮጵያ እያለ ፣ ለብቻው ተለይቶ እየተደቆሰ፣ እየጠፋ በመሆኑ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሄረተኞችና የትግራይ ብሄረተኞች የዘር ብሄረተኝነታቸውን ትተው፣ የዘር ህገ መንግስት ይቀየር፣ የዘር አወቃቀር ይፍረስ ወደሚለው አቋም ከመጡ፣ ማንም ነጋሪ ሳያስፈልጋቸው የአማራ ብሄረተኞችም ነጭ ባንዲራው ይዘው ነው እኛም አለን ብለው እየተጣደፉ የሚመጡት፡፡ ለምን?  ውስጣቸው ያለው የአንድነት መንፈስ ስለሆነ፡፡
እነዚህ የአማራ ስብስቦች፣ አጀንዳቸው አጀንዳዬ ነው፡፡ በመሆኑም ለአማራ ድርጅቶች፣ ለጉባዬው ተሳታፊዎች በዚህ አጋጣሚ ያለኝን አጋርነት እገልጻለሁ፡፡
እኔ አማራ አይደለሁም፡፡ ዉህድ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሌሎች ብዙ ማንነቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ያ መብታቸው ነው፡፡ እኔ ግን ፣ “አማራነትም ኦሮሞነት ይቅርብኝ፣ አይመቸኝም፣ ኢትዮጵያዊነቴ ይበቃኛል” ባይ ነኝ፡፡ እንደኔ የዜግነት ፖለቲካ ነው የምናራምደው የምንል፣ ዉህድ ኢትዮጵያዊ የሆንን፣ በተለይም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ እንደገና ደግሞ በኦህዴዶች እየተደቆስን ያለን፣ በተለይም እንደ ጉራጌ፣ ወላይታ ካሉ የደቡብ ክልል ማህበረሰባት የወጣን፣ አንድ ነገር በሚገባ ጠንቅቀን ማወቅ ያለበን፣ የአማራዎች እንቅስቃሴ ለኛም ጥቅም የሚያመጣ እንቅስቃሴ መሆኑን ነው፡፡ የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የአዲስ አበባ ልጆች ወዘተ ትግል፣ ከአማራው ትግል ጋር መናበብና መቀናጀት አለበት፡፡
አንድ ነገር አንርሳ፣ ዉህድ ኢትዮጵያዉያን፣ የአዲስ አበባ ልጆች፣ አማራ ነን ባንልም፣ ወደድንም ጠላንም፣ በተረኞችና በዘረኞች ‘አማራ” ተደርገን ነው የምንቆጠረው፡፡ የምገደለው፣ የምንጨፈጨፈው፣ የምንፈናቀለው፡፡ ጉራጌዎች፣ ወላይታዎች ወዘተ ትናንሽ ‘አማራዎች፡ ነው የሚባሉት፡፡ እነ አብይ አህመድ የወላይታና የጉራጌ ክልል አንፈቅድም ያሉት፣ ለምን ይመስላቹሃል? ከአማራ ጋር የሚሰለፉ ናቸው በሚል ነው፡፡