የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቀረበበትን ክስ በፍፁም እንደማይቀበለው አስታወቀ

  • የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቀረበበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ በፍፁም እንደማይቀበለው አስታወቀ
  • መግለጫው በአገሪቱ አንድን ወገን በሌላኛው ላይ ለማነሣሣት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ቆስቋሽ መግለጫ ነው ብሎታል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተከስቷል ሲል የደረሰበትን ድምዳሜ የኢትዮጵያ መንግሥት በፍፁም እንደማይቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር በጋራ ካደረጉት ምርመራ አንፃር ሲታይ ምንም አዲስ ግኝት ያልተካተተበት ነው ብሏል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያቀረበበትን ባዶ ውግዘት በፍፁም እንደማይቀበለው ገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ አንድን ወገን ብቻ መወንጀል ላይ ያነጣጠረ መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫ ማስታወቁን ኢብኮ ዘግቧል።

በሌላ በኩል፤ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮችን ለመለየት ብሔራዊ ምክክር ለመጀመር በተዘጋጀችበት ወቅት ላይ የወጣ በመሆኑም መግለጫው ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ብሎታል።

በተጨማሪም “የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ይህን መግለጫ ለማውጣት ያሰበበት ዓላማ ምንም ይሁን ምን መግለጫው በአገሪቱ አንድን ወገን በሌላኛው ላይ ለማነሣሣት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ቆስቋሽ መግለጫ ነው።” ሲል የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር