“ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ስለማላስብ ፍ/ቤት አልቀርብም” አቶ ስንታየሁ ቸኮል

▪️ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ስለማላስብ ፍ/ቤት አልቀርብም” አቶ ስንታየሁ ቸኮል
▪️ አቶ ደስታ ለሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም ተቀጥረዋል
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮል ለዛሬ መጋቢት 8/2015 ዓ.ም መቀጠራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።ሆኖም ዛሬ የግፍ እስረኛው አቶ ስንታየሁ፤ ፍ/ቤቱ ከዚህ ቀደም የሳቸውን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንደሌለው የተናገረውን በመጥቀስ “ፍ/ቤቱ ጉዳዬን ለማየት ሥልጣን የለኝም እያለ፤ ፍትሕ አገኛለሁ ብዬ ስለማላስብ ችሎት አልቀርብም” ብለዋል።
አቶ ስንታየሁ በመንግሥት ኃይሎች አፈና የተፈፀመባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናኖቿን ምእላ እንዲያደርጉ ባዘዘችው መሠረት፤ በጎፋ ገብርኤል ተገኝተው የምእላ ስርዓቱን በመፈፀም ላይ ሳሉ ነበር። የግፍ እስረኛው በፀጥታ ሀይሎች ከታፈኑ ዛሬ 1 ወር ከሳምንት ሆኗቸዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ያልቻሉ ሲሆን፤ በቀጠሯቸው መሰረትም ሆስፒታል መቅረብ አልቻሉም። ይህም የኦህዴድ-ብልፅግና መንግሥት ፍፁም እኩይነት አንዱ ማሳያ ነው።
ሌላው በዛሬው እለት ፍ/ቤት የቀረቡት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የክ/ከተማ አመራር እና የዲስፕሊን ኮሚቴ አባሉ አቶ ደስታ መታፈሪያ ለሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም ተቀጥረዋል። የግፍ እስረኛው አቶ ደስታ መታፈሪያ ዛሬ በአራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ በዋስ እንዲለቀቁ በጠበቃቸው አቶ ሳምሶን በኩል ተከራክረዋል። ችሎቱም ፖሊስ ያቀረበውን የአቶ ደስታን መዝገብ ባለማየቱ፤ መዝገቡን አይቶ በዋስትናው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም ቀጥሯል።