የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።

አንቶኒዮ ብሊንከን አዲስ አበባ ገቡ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

ብሊንከን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ጉብኝታቸው ለማድረግ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም ለማስፈን እና የሽግግር ፍትሕን ለማረጋገጥ በፕሪቶሪያ በተፈረመው፣ በቋሚነት ግጭት የማቆም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

ብሊንከን ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪም፤ ከሰብዓዊ ድርጅቶች እና ከከሲቪክ ተቋማት ጋር በሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭት፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ እንደሚነጋገሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ጋር እንደሚገናኙ የተገለጸ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁም ወደ ኒጀር እንደሚያቀኑ ተነግሯል።