የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት አገልግሎቶች ላይ ጥሎት የነበረውን ጊዜያዊ እግድ አነሳ

[addtoany]

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙት 11 ክፍለ ከተሞች፤ ለሁለት ወር ገደማ ያህል ታግደው የቆዩ የመሬት አገልግሎቶችን በድጋሚ መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ። የከተማዋ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፤ በመሬት አገልግሎቶች ላይ ተጥሎ የቆየውን “ጊዜያዊ እግድ” ከዛሬ ጀምሮ ማንሳቱን አስታውቋል።

“ጊዜያዊ እግዱ” የተነሳው፤ የከተማዋ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ለአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ዛሬ ረቡዕ የካቲት 29፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ነው። የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ፤ እግዱን መነሳቱን ለክፍለ ከተሞች በደብዳቤ ማሳወቃቸውን  ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ እግዱን ያስተላለፈው፤ ሁለት “መሰረታዊ መነሻዎችን” ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ዶ/ር ቀነዓ ተናግረዋል። የቢሮ ኃላፊው በቀዳሚነት የጠቀሱት፤ በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን “የመሬት ወረራ እና ህገ ወጥነትን” ነው።

ይህ ምክንያት ቢሮው ለክፍለ ከተሞች በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በጻፈው ደብዳቤ ላይም የተነሳ ጉዳይ ነው። ቢሮው በዚሁ ደብዳቤው “የመሬት ወረራ እና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች” መኖራቸውን እንደለየ አስታውቆ፤ ችግሩን ለመፍታት “ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ” ተገቢ መሆኑን ገልጾ ነበር።

የመሬት እግዱ ለመተላለፉ ሁለተኛው ምክንያት “መንግስት የጀመረው የጸረ ሙስና ትግል” መሆኑን ዶ/ር ቀነዓ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ይህንን የመንግስትን ዘመቻ ተከትሎ “መሬት፣ ንብረት እና የተለያዩ ሀብቶች አላግባብ እንዳይሸሹ” ለማድረግ እገዳው እንደተጣለ አስረድተዋል።

በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች “በማዕከል ከሚወሰኑ እና ለወደፊትም በልዩ ሁኔታ ከሚወሰኑ በስተቀር” ማንኛውም የመሬት አገልግሎት “በጊዜያዊነት” ታግዶ ቆይቷል። የከተማዋ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ዛሬ ለክፍለ ከተሞች በጻፈው ደብዳቤ ግን “ለእገዳው ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች መፍትሔ” ማግኘታቸውን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ በበኩላቸው “[ችግሩ] ሙሉ ለሙሉ ተፈቷል ባይባልም፤ አሁን ከሞላ ጎደል መንግስት የተወሰነ ማስተካከያ ስለወሰደ እገዳው ሙሉ ለሙሉ ተነስቷል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ሁሉም እገዳ ተነስቷል። ህጋዊ አሰራሮች ተከትሎ ማንም የመሬት አገልግሎትን ከመንግስት ሊያገኝ ይችላል” ሲሉም ዶ/ር ቀነዓ አክለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ዛሬ በጻፈው ደብዳቤ፤ በየክፍለ ከተሞቹ የሚገኙ ጽህፈት ቤቶች “ህጋዊ አሰራሮችን በመከተል” እና “የሚቀርቡላቸውን መረጃዎች ትክክለኝነት በማረጋገጥ” የመሬት አገልግሎትን እንዲያስቀጥሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ክፍለ ከተማዎቹ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ዶ/ር ቀነዓ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)