ላለፉት 19 ወራት ስራ አቁሞ የቆየው አክሱም ዩኒቨርስቲ በጦርነት ሳቢያ 15 ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት ደረሰበት

በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አራት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነው አክሱም ዩኒቨርስቲ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የደረሰበት ጉዳት 15 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት አስታወቀ። ላለፉት 19 ወራት ትምህርት መስጠት አቁሞ የቆየው ዩኒቨርስቲው፤  ሊያከናውነው ላቀደው “ዳግም ግንባታ” የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።

በ2006 ዓ.ም የተመሰረተው አክሱም ዩኒቨርስቲ በስሩ ባሉት ስድስት ኮሌጆች እና ሁለት ኢንስቲትዩቶች ተማሪዎችን ከመላው ሀገሪቱ ሲቀበል ቆይቷል። አክሱም ዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ተማሪዎቹን ያስመረቀው ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጀመር በኋላ በየካቲት 2013 ዓ.ም ሲሆን፤ በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ትምህርት መስጠት ማቋረጡን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ብርሃነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው በጦርነቱ ሳቢያ በደረሰበት “ውድመት እና ዘረፋ” የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር የሚያስችሉት ቁሳቁሶች እና መሳሪያዎች ማጣቱን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ሙሉ ለሙሉ እንደተዘረፉ እና እንደወደሙ ከጠቀሷቸው የዩኒቨርስቲው ንብረቶች ውስጥ፤ ኮምፒውተሮች፣ የላብራቶሪ መሳሪያዎች፣ ሰርቨሮች እና የቢሮ በሮች ይገኙበታል። ዩኒቨርስቲው ከጦርነቱ በፊት የነበሩት 60 ገደማ ተሽከርካሪዎች “ተዘርፈው እና ተቃጥለው”፤ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው “አንድ መኪና ብቻ” መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።

ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት አስመልክቶ አክሱም ዩኒቨርስቲ በጥር ወር ላይ ባደረገው ዳሰሳ፤ የደረሰው ውድመት 15 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ መገመቱን ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ አስረድተዋል። ዩኒቨርስቲው ጉዳት የደረሰባቸውን ንብረቶች “በተወሰነ መልኩ” በመተካት ወደ ስራ ለመግባት ማቀዱንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ዩኒቨርስቲው ለሚያከናውነው “ዳግም ግንባታ እና ጥገና ስራ”፤ የገንዘብ እና የማቴሪያል ድጋፍ እንዲደረግለት ትላንት ሰኞ የካቲት 27፤ 2015 ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል።

አክሱም ዩኒቨርስቲ የድጋፍ ጥሪውን ያቀረበው፤ ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር በቀል አጋር ድርጅቶች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነው። ዩኒቨርስቲው በዚህ ጥሪ የሚያገኘውን ድጋፍ በፌደራል መንግስት ከሚመደበለት በጀት ጋር በማጣመር በአጭር ጊዜ ውስጥ የመማር ማስተማር አገልግሎቱን ለመስጠት አቅዷል።

“[ቁሳቁሶችን] በተወሰነ መልክ ቅድሚያ እየሰጠን ካስገባን፤ የግዢ ሂደቱ ፈጣን ከሆነ፤ ተማሪዎችን በሶስት ወር ውስጥ ማስገባት እንችላለን” ሲሉ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት የተቋሙን እቅድ ገልጸዋል። በትግራይ ክልል የሚኖሩ እና ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ያቋረጡ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን “ትምህርት ማስጨረስ” ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አክለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ እስካሁን ከፌደራል መንግስት በጀት ባይለቀቅለትም፤ በስሩ ለሚገኘው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 43 መምህራንን ለመቅጠር ከሁለት ሳምንት በፊት ማስታወቂያ አውጥቷል። የቅጥር ሂደቱ የሚፈጸመው በትምህርት ሚኒስቴር ተፈቅዶ፣ በጀት ሲለቀቅ መሆኑን የሚያስረዱት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ፤ ማስታወቂያው እንዲወጣ የተደረገው “ሂደቱን ለማፋጠን” መሆኑን አብራርተዋል።

ከፌደራል መንግስት የሚለቀቀው በጀት፤ ለዩኒቨርስቲው ሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈል እና ትምህርት ለማስጀመር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። አራት ሺህ ገደማ የሚሆኑት የዩኒቨርስቲው መምህራን እና ሰራተኞች ከሐምሌ 2013  ዓ.ም. ወር ጀምሮ ደመወዝ አለማግኘታቸውን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)