ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በሚል በቀበሌው መስተዳድር ጥሪ የተደረገላቸው የሲዳማ ብሄር ተወላጅ አርሶአደሮች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነሰቦ ወረዳ በደረሰ ጥቃት በትንሹ 12 ሰዎች ተገደሉ ፡፡ ነዋሪዎች እንዳሉት ጥቃቱ ባለፈው ዓርብ የተፈጸመው በወረዳው ቦጬሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ነው ፡፡ ከሟቾቹ አብዛኞቹ የሲዳማ ብሄር ተወላጅ አርሶአደሮች መሆናቸውን በሥፍራው ነበርን ያሉ አይን አማኞች ለዶቼ ቬለ/DW/ ተናግረዋል ፡፡ ግድያው የተፈጸመው ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በሚል በቀበሌው መስተዳድር ጥሪ ከተደረገላቸው በኋላ መሆኑን ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡

በተሰበሰበው ነዋሪ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተከፈተው ተኩስ ሦስት ሰዎች ወዲያው መገደላቸውንና የተቀሩት አሥር ሰዎች ደግሞ በመሸሽ ላይ እንዳሉ በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ነው ከዓይን አማኞቹ አንዱ ለዶቼ ቬለ DW የገለጹት፡፡  በጥቃቱ ቡርቃ ቡታሮ እና ሳሙኤል ቡታሮ የተባሉ ሁለት ወንድሞቻቸው እንደተገደሉባቸው ለዶቼ ቬለ የገለጹት ቴሶ ቡታሮ የተባሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው « ጥቃቱ የግፍ አገዳደል ፤ ሁኔታውም የዘር ጭፍጨፋ ይመስላል»’ ብለዋል ፡፡

በጥቃቱ በጥይት ተመተው የቆሰሉ በርካታ ሰዎች በአጎራባች የሲዳማ ክልል በሚገኘው የጭሪ ወረዳ ጤና ጣቢያ መወሰዳቸውን የዓይን አማኞቹ ገልጸዋል ፡፡ የሐዋሳው ወኪላችን ሽዋንግዛው ወጋዩሁ ስለጥቃቱ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን መስተዳድር እና የሲዳማ ክልል የፀጥታ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል ፡፡ ይሁንእንጂ በሁለቱም በኩል የሚገኙ የሥራ ሃላፊዎች «ሁኔታውን እያጣራን እንገኛለን» የሚል አጭር ምላሽ በመስጠታቸው እስከአሁን ሥለጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በሲዳማ ክልል የጭሪ ወረዳ ጤና ጣቢያ ሐኪም ግን በቁጥር ለመጥቀስ ቢቸገሩም በጥይት የተመቱ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው ከመጡ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡

በተጨማሪም እሳቸው በሚሠሩበት የድንገተኛ ክፍል ቀላል ቁስለት የደረሰባቸው 28 ተጎጂዎች ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን 11 ሰዎች ደግሞ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሀዋሳ ከተማና እና ቦና ወረዳ ሆስፒታሎች መላካቸውን ተናግረዋል ፡፡