በደቡብ ክልል ለሚከናወነው ሕዝበ ውሣኔ ድምጽ መስጠት ተጀመረ

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር የሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) አንድ ላይ አዲስ ክልል ለመመስረት ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ ድምፅ የመስጠቱ ሂደት በዛሬው ዕለት በይፉ ተጀምሯል።

በየአካባቢዎቹ የሚገኙ መራጮች፣ ወደ ጣቢያዎቹ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በማቅናት፤ በኢትዮጵያ 12ኛውን አዲስ ክልል ለመመስረት በሚደረገው ሕዝበ ውሳኔው ላይ ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ጣቢያዎቹ እስከ ዛሬ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ክፍት የሚሆኑ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መራጮች በተጠቀሰው ሰዓት ወደተመዘገቡበት ጣቢያ በመሄድ ድምፃቸውን እንዲሰጡ አሳስቧል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ማለትም በ31 ማዕከላት ሥር ባሉ 3 ሺሕ 769 ምርጫ ጣቢያዎች ባካሄደው የመራጮች ምዝገባ፤ አጠቃላይ 3 ሚሊየን 028 ሺሕ 770 መራጮች ተመዝግበው የድምፅ መስጫ ካርድ መወሰዳቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ