ሽምግልና ቀልድ ነው!

ሽምግልና ቀልድ ነው!

1) “መንግስት” የተወገዘ ቡድን ብቻ አይደለም የደገፈው። የቤተ ክርስቲያንን ክብር ያወርዳሉ ያላቸውን ሰዎች ሰብስቦ ነው ፕሮጀክቱን እያስኬደ ያለው። የቤተ ክርስቲያንን ህግና ስርዓት መናድ ብቻ አይደለም። የመጨረሻውን ንቀት፣ ጥላቻ ያሳየበት ነው።

2) ሲኖዶሱ ለምኗል። በመንግስት ደረጃ ጥቃት ታውጆበት እንኳን የማሰቢያ ጊዜ ሰጥቷል። መንግስት የተወገዘውን ቡድን ደግፎ የቤተ ክርስቲያን በር ሰብሮ ሲገባ ነው ሰልፍ የጠራው።

3) ቤተ ክርስቲያን የቀራት ነገር የለም። ህጓ ተጥሷል። ተንቃለች። ተጠቅታለች። ልጆቿ ተገድለዋል። ለሽምግልና የሚሆን ክፍተት አልቀራትም። እያንዳንዱን እየሄደችበት ያለው በህጓ መሰረት ነው።

4) መንግስት የተወገዘውን ቡድን የማስቆም ሙሉ አቅም እያለው ሽምግልና ሊጠይቅ አይችልም። መሆን ካለበት የተወገዘው ቡድን በሰራው ወንጀል ተጠይቆ፣ መንግስት ለፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ ሆኖ፣ ቤተ ክርስቲያንንና የህዝብን ቁስል የሚያሽሩ እርምጃዎች ቢወሰዱ ነበር። አያደርጉትም! ማዘናጊያ ብቻ ነው። የትግሉን ርቀት መለኪያ ነው!

ሽምግልና ቀልድ ነው። የቤተ ክርስቲያን በርን እየሰበረ ለሚገባ የተወገዘ ቡድን ድጋፍ የሚሰጥ ኃይል ስለ ሽምግልና ለመጠየቅ ሞራል የለውም። አያምንበትምም። ቤተ ክርስቲያንን ያዋርዱልኛል ያላቸውን ሰዎች ከየትም ለቃቅሞ የማፍረስ ስራ እየመራ ያለ ኃይል ስለ ሽምግልና የሚያወራው ስለጨነቀውና ስላላዋጣው ብቻ እንጅ ሊያምንበት አይችልም።

ቤተ ክርስቲያንንና ህዝብን እናዋርድበታለን ያሉበትን የመጨረሻውን ርቀት ሄደዋል። የቤተ ክርስቲያንንና ህዝብን ክብርና ህልውና የሚያስጠብቀውን የመጨረሻው ርቀት ድረስ መሄድ ያስፈልጋል። በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያን በር እየሰበረ በሌላ በኩል ሽምግልና እየላከ የሚያወናብድ አካል ማወናበጃው እንደማይሰራ ማሳየት የሚቻለው ጥቃቱን ለማስቆም የሚቻለውን የመጨረሻ ርቀት መሄድ ሲቻል ነው።