አጭበርባሪ የተባሉ ዲያስፖራዎች የባንክ አካውንት ታገደ

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ ምንዛሬ ሂሳብ እንዲከፍቱ የተፈቀደበት አሠራር ለሕገወጥ ተግባራት መጋለጡን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አገልግሎቱ መንግሥት ፍቃዱን ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ፣ በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ 85 ግለሰቦችንና ከ22 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በባንክ ማሳገዱን ገልጧል። አገልግሎቱ ተፈጸሙ ካላቸው ሕገወጥ ተግባራት መካከል፣ ውጭ አገር ያልሄዱ ሰዎች ውጭ የሄዱ ማስመሰል፣ ከጥቁር ገበያ የሰበሰቡትን የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይዘው የገቡ ማስመሰል፣ ሐሰተኛ ሰነዶችን ማቅረብ እና በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ ሂሳቦችን መክፈት እንደሚገኙበት አገልግሎቱ ገልጧል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ባንኮች የውጭ አገራት ገንዘብ የሂሳብ ደብተር የሚከፍቱበትን የዳያስፖራ አካውንት ህግና አሠራር የጣሱ የተለያዩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መግለጫ አመላክቷል።
እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ክትትልና ማጣራትም 85 ግለሰቦች የተሳተፉበትና መጠኑ 20 ሚሊዮን 226 ሺህ 583 ዶላር የውጭ አገር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ በማድረግ ለወንጀል ምርመራ መተላለፉን ገልጿል። ከሃገር ውስጥ ሳይወጡ ውጭ ሃገር ሔደው የተመለሱ በማስመሰል ሃሰተኛ ዴክለራሲዮን ማቅረብ፣ እንዲሁም ከውጭ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው በመግባትና ከፍተኛ ገንዘብ ይዘው የገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገወጥ መንገድ መሰብሰብ ለወንጀሉ በማጭበርበሪያ ስልትነት መጠቀማቸውን በመግለጫው ጠቁሟል።

በተጨማሪም የሌላውን ዲክለራሲዮን የራሳቸው በማስመሰል ከሚፈቀደው ውጭ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት መክፈትና ሌሎች ሃሰተኛ ዲክለራሲዮኖችን ለወንጀል ተግባር ስለመዋላቸው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን ገልጿል።ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲያስፖራ አካውንትን በሚመለከት የወጣውን መመሪያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 ጨምሮ የወንጀል ህግን መተላለፋቸውን በመግለጫው ጠቁሟል።

በመሆኑም የወንጀሉ ተሳታፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩ ለወንጀል ምርመራ መተላለፉን አገልግሎቱ ጠቅሶ መሰል ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በመሰል ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ በመገንዘብ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም በመግለጫው አሳስቧል።