የጉራጌ ዞን ያቀረበው ተቃውሞ ጠንከር ብሎ በመምጣቱ የፌዴሬሽን ምክርቤት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል
ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ራሳቸውን ችለው ከወጡ በኋላ የቀሩትን ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን በሁለት የክላስተር ክልል አደረጃጀቶች ሥር የማዋቀር ዕቅድ በመንግሥት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ግን ከአንዳንድ የዞን አስተዳደሮች በኩል ከባድ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡
በዚህ የተነሳ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦና ኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ነው የክላስተር ክልል አደረጃጀትነት ሕዝበ ውሳኔው በጥር ወር የሚካሄደው፡፡
ቀሪዎቹ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮና ሀላባ ዞኖች፣ እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ዕጣ ፈንታ እስካሁን አለየለትም፡፡ ከእነዚህ በአንድ ክላስተር ክልል አደረጃጀት ይካተቱ ከተባሉት መካከል ደግሞ አደረጃጀቱን አጥብቀው የተቃወሙ የዞን አስተዳደሮች በመኖራቸው፣ ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ገና ውሳኔ እየጠበቀ ነው፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ጥያቄው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቅ ይጠበቅበታል፡፡ በአንድ ክላስተር ተደራጁ ከተባሉት መካከል በተለይ የጉራጌ ዞን ያቀረበው ተቃውሞ ጠንከር ብሎ በመምጣቱ የተነሳ፣ በዚህኛው አደረጃጀት ላይ ሕዝበ ውሳኔው ይካሄድ ብሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ ለመምራት መቸገሩ ነው የተነገረው፡፡
ይህም ቢሆን የተለያዩ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችና ወረዳዎች በአንድ ክልል ሰብሰብ ብለው እንዲደራጁ የቀረበው ዕቅድ ከእነ ብዙ ተቃውሞው ወደ መሬት እየወረደ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ተቃውሞው የበለጠ እንዲባባስ እያደረገው ይገኛል፡፡ በተለይ በክላስተርም ሆነ በሌላ መንገድ ከሌሎች ብሔረሰብ አስተዳደሮች ጋር ተሰባስበን ክልል አንፈጥርም ብለው ሲቃወሙ የቆዩ ዞኖች፣ አሁንም በተቃውሟቸው እንደገፉ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከሰሞኑ የፖለቲካ ውጥረቱና ተቃውሞው የጨመረው የጉራጌ ዞን በዋናነት ይገኝበታል፡፡
ከሰሞኑ ብቻ ጉራጌ ዞን የራሱ ክልል ይገባዋል የሚል ተቃውሞ ያነሱ ከ200 በላይ ወጣቶች መታሰራቸውን የአካባቢው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ጉራጌ ለብቻው ክልል እንዲሆን ሲቀሰቅሱና በተለያዩ መንገዶች ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ፖለቲከኞች መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡
የጉራጌ ዞን ዕዣ ወረዳን ወክለው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌን ጨምሮ፣ የጉራጌ ክልልነትን ጥያቄ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ታዋቂ ፖለቲከኞችና ማኅበራዊ አንቂዎች መታሰራቸው ደግሞ ችግሩን እያወሳሰበው እንደሚገኝ ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡
የዞኑ አስተዳደር ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ጥያቄውን ሽፋን በማድረግ ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቆ ነበር፡፡ የዞኑ አስተዳደር በዚህ መግለጫው ለረዥም ጊዜ ሲቀርብ የነበረውን የክልልነት ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችል አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ የለም ብሎ እንደሚያምን አስታውቆ ነበር፡፡ የዞኑ አስተዳደር መግለጫውን ሲቀጥልም፣ ‹‹መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመቀበል ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትና የዞናችን ሰላም ወደነበረበት መመለስ እንዳለበት የዞኑ አስተዳደር ያምናል፤›› በማለትም የክላስተር አደረጃጀቱን ውሳኔ የተቀበለው መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡
የዞኑ አስተዳደር ይህን ቢልም ጥያቄያችን መልስ ሊያገኝ ይገባል ያሉ የጉራጌ ተወላጆች ግን፣ የክልልነት ጥያቄያቸውን ማስተጋባት ሲቀጥሉ ነው የታየው፡፡ ይህን ተከትሎም የደቡብ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዴ በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው ዞኑ በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲመራ መታዘዙን ይፋ አድርገው ነበር፡፡