በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ በኮረም፣ በአላማጣ፣ በአዲግራት፣ በአክሱምና በአድዋ አቅራቢያዎች ውጊያዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ሜዲያዎችም ኮረም፣ ዓላማጣ፣ ማይጠምሩ. በጥምር ጦሩ ስር እንደገቡ እየተናገሩ ነው፡፡ በጥምር ጦሩ በሽሬ ዙሪያ ሆኖ ፣ የከተማ ውጊያ ላለማድረግ ወደ ከተማዋ አልገባም፡፡ ከህወሃት ቁጥጥር ውጭ በወጡ አካባቢዎች የመንግስት አገልግሎቶችን ለማስጀመር እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡
ሕወሃቶች፣ “ጦርነቱ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ከተሸነፍን ጠላቶቻችን ጄኖሳይድ ይፈጽሙብናል፣ ያጠፉናል” የሚል ቅስቀሳ እያደረጉ፣ ሕዝቡን በነቂስ በክተት እንዲዋጋ እያደረጉት ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች እያፈሱ ነው፡፡ ሆኖም ብዙ የተሳካላቸው አይመስልም፡፡
በተለይም በሽሬ መስመር ያለው ሁኔታ እንዳሰቡት ስላልሆነ፣ የበለጠ ጥፋት ከሚከሰት ፣ ብዙዎቻችን ስንጠይቅ የነበረውን ሃሳብ፣ የማርያም መንገድ ተከፍቶላቸው፣ በሰላም የሕወሃት አመራሮች ከአገር ወጥተው ፣ ጦርነቱ እንዲቆም የማድረጉ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች እያየን ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች የማሪያም መንገድ ስንል የሚናደዱ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ አሁንም ሕወሃት የወታደራዊ የበላይነት አላት ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡ ትላንት ሕወሃቶች “ኮሪዶር እናስከፍታለን፣ ወልቃይትን እንይዛለን፣ ከበባዉን እንሰብራለን” ብለው በጉልበታቸው ተማምነው ሲናገሩት የነበረውንና አሁን ሜዳ ላይ ያለውን ወታደራዊ ሁኔታ ማነጻጸር የተሳናቸው፣ የትግራይ ከተሞች እንደ ማሪዮፖልና አሌፖ ሊሆኑ እንደሚችሉ የዘነጉ ናቸው፡፡ እስካሁን ያለቀው ተጋሩ ሳያሳስባቸው ከዚህ በኋላ በሺሆች እንዲያልቁ፣ የህወሃት መሪዎች እስከ መጨረሻ ጠብታ እንዲዋጉ እየጠየቁ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡
ሌሎች ደግሞ የህወሃት መሪዎች ተይዘው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፣ ሕወሃት ሙሉ ለሙሉ መደምሰስ አለባት፣ ከነርሱ ጋር ምንም አይነት ድርድር ሆነ ውይይት አያስፈልግም የሚሉ አሉ፡፡
እነዚህ ወገኖች ከሁለት አመት በፊት የነበረውን የረሱ ሰዎች ናቸው፡፡ ሕወሃቶች ከፈለጉ መሽገው መዋጋት እንደሚችሉ የዘነጉ ናችው፡፡ “ሽሬ ደጅፍ ለመድረስ ከሁለት ወራት በላይ ከፈጀ፣ አስር ሺሆች ከሁሉም ወገን ካለቁ፣ መቀሌ ለመግባት ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል፣ እዚያ እስኪደረስ ምን ያህል ሰው ያልቃል ?” የሚለውን ከግምት ማስጋባት የተሳናቸው ናቸው፡፡
እርሱ ብቻ አይደለም፣ መቀሌ ሲገባ ፣ እነ ደብረ ጽዪን ተይዘው ወይንም ተገድለው፣ የነርሱ ተከታይ ወጣቶች ሸፍተው የሽምቅ ውጊያዎች ሊያደረጉ እንደሚችሉ ማሰብ ያቃታቸው ናቸው፡፡ ከሁለት አመት በፊት ሕወሃት ዱቂት ሆናለች ተብላ ነው እንደገና ደብረ ሲና መድረሷን የረሱ ናቸው፡፡
ከዚህ በኋላ የአስር ሺሆች ሕይወት ማዳን ከተቻለ፣ ዘላቂ ሰላም ካመጣ፣ ለጥቂት የሕወሃት መሪዎች የማሪያም መንገድ መከፈቱን ከተቃወምን፣ በቀለኞች በጥላቻ የተሞላን እንጂ፣ ለሰብዓዊነት ክብር የሌለን መሆናችንን ነው የሚያሳየው፡፡
ወገኖች ጊዚያዊ ስሜታችንን ሳይሆን ለዘለቄታው የሚበጀውን ነው ማሰብ ያለብን፡፡ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በድህነት የማቀቀ፣ ወደ ኃላ የቀረ፣ በኢትዮጵያዉያን ደም የጠገበ፣ ሰላምና ብልጽግና የራቀው አካባቢ ነው፡፡ ያ አካባቢ ትግሬ፣ አማራ በሚል የተረገመ ፖለቲካ እርግማን ውስጥ የነበረና ያለ አካባቢ ነው፡፡ ይህ አካባቢ መሰረታዊ ማሀበራዊ ፈውስ ያስፈልገዋል፡፡ በፍቅር፣ በይቅር መባባል፣ በመያያዝ። በአንድነት፣ ትግሬ አማራ ባለመባባል ፣ አብሮ በማደገድ ከተዘፈቀበት የድንቁር፣ የጥላቻና የድህነት አዘቅት መውጣት መጀመር አለበት፡፡