ምንሊክ ሳልሳዊ ፡ በሰንበት ምድር የመንግስት የፕሮፓጋንዳ ማሽኖች ወሬያቸው ሁሉ ስንዴ ሆኖ ውሏል። ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትጀምራለች ሲሉ መናገር የማይደክማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሆነ የስንዴ ማሳ ውስጥ ሆነው ጅቡቲ ላይ የቆመው የእርዳታ ስንዴ መርከብ ተራግፎ ሳይጨርስ ንግግር አደረጉ። ይህ የምስል እና የንግግር ፖለቲከ ከመነገሩ በፊት ቢታሰብበት መልካም ይመስለናል። ከተረጂነት መውጣት የሚቻለው ሃገርንም ማስከበር የሚቻለው የውስጥ ችግርን በሚገባ ፈትቶ ሕዝቡ በምግብ እህል ራሱን እንዲችል አድርጎ ነው እንጂ የውስጥ ሰብዓዊ እና ሌሎች ቀውሶችን ተሸክሞ ሳያራግፉ ስንዴን ወደ ውጪ እንልካለን የሚል የፕሮፓጋንዳ ድርደራ አያዋጣም።
ከሁለት ቀን በፊት ዩክሬን ለሶማሊያና ለኢትዮጵያ ዜጎች የረዳችዉን ስንዴ ውጪ የሸፈኑት ጀርመን እና ፈረንሳይ መሆናቸው ታውቋል የሚል ዜና ሰምተናል። ዜናውበሩሲያ ወረራ ክፉኛ የወደመችዉ ዩክሬን ለረሐብ ለተጋለጡት ለሶማሊያና ለኢትዮጵያ ዜጎች 50 ሺሕ ቶን ስንዴ ረድታለች።በአዲስ አበባ የጀርመን ኤምባሲ በፅሁፍ ባሰራጨዉ መግለጫ ስንዴዉን ወደ ሁለቱ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት ለማጓጓዝና ለማሰራጨት የሚያስፈልገዉን ወጪ ጀርመንና ፈረንሳይ ከፍለዋል። ይላል።
በረሃብ ችግር ውስጥ ያለ ሕዝብ ይዘን ወደ ውጪ ስንዴ እንልካለን ማለት በሕዝብ ጉሮሮ ላይ እንደመቀለድ አይቆጠርም ? ወይንስ ፑቲን እንዳሉት ስንዴው በኢትዮጵያ ስም ወጥቶ ወደ አሜሪካ ነው የተሸጋገረው ? የአለም የምግብ ድርጅትስ ለኢትዮጵያ 14 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስንዴ ረዳሁ ያለውስ እንዴት ነው ነገር ? መንግስት ለሽያጭ ከመሮጡ በፊት ሕዝቡ በምግብ እህል ራሱን ለመቻሉ ማረጋገጫ ሰቷል ? ……………. እነዚህን እና ሌሎች የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ነው። መልስ ካሌለ መንግስት ያስለመደንን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እየጋነው ነው ማለት ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። የስንዴው ፖለቲካ በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል። ቀድሞ ከማውራት ሰርቶ ማሳየት የተሻለ ነው። #MinilikSalsawi