ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

” አስክሬኑ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ሆስፒታል ተልኳል ” – ፖሊስ

ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

እንደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ከሆነ ፤ ድምፃዊው ዛሬ ጠዋት ላይ ሕመም ተሰምቶት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኩራ ክ/ከተማ ወደ ሚገኝ አንድ የሕክምና ማዕከል ለሕክምና መሄዱና ሕክምና ማድረጉን ከቆይታ በኋላም ህይወቱ እንዳለፈ ታውቋል።

ማዲንጎ ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት እንዳልነበረበት ጓደኞቹ በተገኙበት ቢረጋገጥም አስክሬኑ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ሆስፒታል መላኩን ፖሊስን ዋቢ አድርጎ ኢብኮ ዘግቧል።

የድምፃዊው ወዳጆች በበኩላቸው ፤ ማዲንጎ ህመም ተሰምቶት እራሱ መኪናውን እያሽከረከረ ወደ ህክምና ስፍራ መሄዱን ከዛ በኃላ ህይወቱ እንዳለፈ ጠቁመዋል።

ተወዳጁ ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ማንነበር ?

– ማዲንጎ የተወለደው ጎንደር አዘዞ ሲሆን ልክ በ3 ወሩ ወላጆቹ ደብረ ታቦር መግባታቸውን ተከትሎ በደ/ታቦር ነው ያደገው።

– ማዲንጎ አፈወርቅ ያደገው በጦር ቤት ውስጥ ነው፤ እናት እና አባቱ “ተገኔ” /የኔ ጠበቃ/ ነበር የሚሉት፤ ወላጆቹ ያወጡለት ስም “ተገኔ” ነው። ማዲንጎ የሚለውን ስም ያገኘው በወታደር ቤት ውስጥ እየሰራ እያለ ነው፤ ከዛ በኃላ መጠሪያው ሆኖ ቀጥሏል።

– በልጅነቱ የሙዚቃ ፍቅር ያደረገበት ማዲንጎ ከደብረ ታቦር ወደ አዘዞ በተመለሰበት ወቅት በ7ኛ ክፍለ ጦር ካምፕ ውስጥ በ603ኛ ኮር ውስጥ ያለ የሙዚቃ ቡድን ልምምድ ሲያደርግ በመግባት ዘፈን እንደሚችል በመግለፅ እድል እንዲሰጠው ይጠይቃል፤በኃላም እድል ተሰጥቶ የኤፍሬም ታምሩን ሙዚቃ ከተጫወተ በኃላ አድናቆት በማግኘቱ ተቀባይነት አግኝቶ በዛው ሊቀጥል ችሏል።

– ማዲንጎ ከጦሩ ከወጣ በኃላ በ1982 ዓ/ም አካባቢ ገና በ12 ዓመቱ በባህር ዳር የሙዚቃ ስራዎችን በማቅረብ አንድም ድምፃዊ የመሆን ህልሙን መስመር ያስያዘበት በሌላ በኩል ገቢ በማግኘት እራሱንና ቤተሰቦቹን ማገዝ የቻለበትን ሁኔታ መፍጠር ችሏል።

– ማዲንጎ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኃላ በተለያዩ የሙዚቃ ክበቦች የተለያዩ አንጋፋ ድምፃዊያንን ስራዎች ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን በኃላም የራሱን ስራዎች (ነጠላና የአልበም ስራዎች) ለአድናቂዎቹ አቅርቧል።

– ማዲንጎን በስራዎቹ የሚያውቁት ወዳጆቹን ዜማ በመያዝ ችሎታ፣ ሙዚቃን አሳምሮ በመጫወትና የአድናቂዎቹን ቀልብ በመሳብ የተካነ በማህበራዊ ህይወቱም ተግባቢ፣ ቅንና ተጫዋች እንደሆነ ይመሰክሩለታል።

(ከጨዋታ እንግዳ ፕሮግራም/ከቅርብ ወዳጆቹ የተገኘ መረጃ)

ተወዳጁ ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።