“ይሄ ተያዘ፣ ያ ተለቀቀ” ለሚል ስሜታዊ ፕሮፖጋንዳ ጊዜ መስጠቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ የማዘንና የመደሰት የዥዋዥዌ ጨዋታ ውስጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም፡፡
ይልቅ ሁላችንም ልንጠይቃቸው፣ ሊያስጨንቀን የሚገቡ ጉዳዮችና ጥያቄዎች አሉ፡፡ “ተለቀቀ፣ ተያዘ” የሚል ጨዋታ መቼ ነው የሚቆመው ? ጦርነቱ በድርድር ይሁን በአንዱ አሸናፊነት መቼ ነው የሚጠናቀቀው ? ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎና እፋርም ያለው ህዝብ መቼ ነው ሰላም የሚያገኘው ? ወዘተ የሚሉት ናቸው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ፣ “መንግስት አለ” ነው የሚባለው፡፡ ራሱን የብልጽግና መንግስት ብሎ የሚጠራ፡፡ ሆኖም በዚህ መንግስት አገራችን ኢትዮጵያ ያየችው ቢኖር ረሃብ፣ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጻዳር ወጀሎች፣ የኑሮ ዉድነትና በአገራቸውን የዜጎች ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡ ይህ መንግስት ህዝብን የሚዋሽ፣ ለህዝብ ስቃይና መከራ ደንታ የማይሰጠው መንግስት ነው፡፡ በስሜኑ የአገራችን ክፍል ላለው ስቃይም መከራ፣ ደም መፋሰስና እልቂት በዋናነት ተጠያቂው የብልፅግና መንግስት ነው፡፡
1ኛ ብዙ ጊዜ ፣ በጦርነት ህወሃትን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፍ ሲቻል፣ ጫፍ ሲደረስ፣ ተኩስ አቁሙ እያሉ፣ ህወሃትን ማዳን ብቻ ሳይሆን እንደገና እንድትጠናከር እድል የሰጡና እየሰጡ ያሉት ብልጽግናዎች ናቸው፡፡ በቀዳሚነት የኦህዴድ/ብልጽግና፡፡
2ኛ ህወሃቶች ለድርድር ፍቃደኛ እንዲሆኑ፣ ቢያንስ ሁሉንም ባይሆን ግማሹን ህወሃቶች የጠየቁትን ፣ የአብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት መሟላት ይችል ነበር፡፡ መብራት: ኔትዎርክ የመሳሰሉት ማስጀመር ችግር አልነበረም፡፡ ለህዝብ የሚያስብ መንግስት ቢሆን ኖሮ ህወሃቶች ሳይጠይቁ ማድረግ ነበረበት፡፡እነዚህን መሰረታዊ አገልግሎቶች ማሟላት ቢቻል ኖሮ ምን አልባት ህወሃት ወደ ውጊያ እንዳትሄድ ህዝቡም ጫና ያደርግባት ነበር፡፡ ህወህት ጦርነቱን እንድትቀጥል ሰበብ ነው የሰጧት፡፡
በነገራችን ላይ የሰሜኑ የአገራችን ግዛት በጦርነት ሰደድ እሳት ውስጥ ገብቶ ባለበት ወቅት፣ ራሱን ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ብሎ የሚጠራው ፣ አብይ አህመድ፣ በአልጄሪያ ጉብኘት ላይ ነው፡፡ አንድ ወቅት መስቀል አደባባይ ሕዝብ ሰብስባ ህወሃትን ስታወግዝ የነበረችውና ከዚያ ከተነሳ እነ ፋሲል የኔዓለም “ጣይቱ” ብለው የጠሯት አዳነች አበቤ ፣ በአዲስ አበባ ፓርክ እያስመረቀች ነው፡፡
ብዙዎች የአብይ መንግስትና የኦህዴድ ፖለቲከኞች በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም እንዲኖር የሚፈልጉ አይደለም ይላሉ፡፡ እውነታቸውን ሳይሆን አይቀርም፡፡ የትግራይና የአማራ ክልል ማህበረሰባት እየተገዳደሉ፣ ሰሜኑ በጦርነቱ ምክንያት እየቆረቆዘ፣ ህዝቡም እየደኸየ፣ እነርሱ ተረጋግተው በአዲስ አበባ እየተምነሸነሹ ለመቀጠል የፈለጉ ይመስላል፡፡ ምን አልባትም ጦርነቱ እነርሱ ደጃፍ ፣ ሸዋ ሲደርስ፣ ልንዘምት ነው ብለው ሊነሱም ይችላሉ፡፡
የሚያሳዝነው ተጋሩዎችም ሆነ አማራዎች፣ ይሄን መገንዘብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ወልቃይትም ራያ እያሉ በጋራ፣ ተከባብረው መኖር ለሚችሉበት መሬት፣ እንደ ጠላት እየተያዩ ነው፡፡ ለነ ወልቃይት፣ ለነ ራያ ጉዳይ ቀላል ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መፍትሄ ነበረ፡፡ እልህ ስላለ፣ “የትግሬ መሬት፣ የአማራ መሬት” የሚል መርዛማ የዘር ፖለቲካ የብዙዎችን አይምሮ ስላቆሸሸ እንጂ፡፡ መነጋገር ሲቻል መተላለቁ አሳዛኝ ነው፡፡ በተለይም ህወሃቶች ጋር ያለው ግትርነት፣ ከአማራው ጋር መነጋገርን በጣም አስቸጋሪ ነው ያደረገው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በስሜን ወሎና አፋር ምድር ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ነው፡፡ መቀሌ ያሉት አዛዦች በአስቸኳይ ታጣቂዎቻቸውን ከወሎና አፋር ማስወጣት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ ከአንድ አመት በፊት ሸዋ ደርሰው ከጥፋት በቀር ያመጡት ምንም አይነት ፋይዳ አልነበረም፡፡ አሁንም ክያኔው አይለይም፡፡ ለመገደል ሲመጡ እነርሱም ይገደላሉ፡፡ የአፋርና የአማራ ክልል ማሀበረሰብ አምሮ ይዋጋቸዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር ተዋግቶ ደግሞ ያሸነፈ የለም፡፡
ጦርነት ይቁም ! አሁኑኑ !!!!