በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመማር የሚፈልጉ ተማሪዎች በቅድሚያ እውቅና ስለመኖሩ ሊያረጋግጡ ይገባል

በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመማር የሚፈልጉ ተማሪዎች በቅድሚያ እውቅና ስለመኖሩ ሊያረጋግጡ ይገባል ሲል የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አሳሰበ። በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የግልና የመንግስት ተቋማት ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን ተማሪዎችም የሚመዘገቡበትን ተቋምና የሚማሩትን የትምህርት አይነት በመምረጥ ለመማር ይሰናዳሉ። በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ፤ ተማሪዎች ከምዝገባ በፊት መረጋገጥ ያለባቸው መስፈርቶች ስለመኖራቸው ይዘረዝራሉ። የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሲኦሲ ሳይፈተኑ የሚማሩና እውቅና ሳይኖራቸው የሚያስተምሩ ተቋማት መኖራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የትምህርት ጥራት ችግርን ለማስቆም ባለስልጣኑ በርካታ የአሰራር ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልጸው የሁሉም ትብብርና እገዛም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ለዚህም አጠቃላይ ህብረተሰቡ፣ ተማሪዎችና ወላጆች ህጋዊ አሰራሩን ተከትለው የማያስተምሩና እውቅና የሌላቸውን ተቋማት መለየት አለበት ብለዋል። በመሆኑም ተማሪዎች በተቋማት ለመመዝገብ ሲፈልጉ ወደ 9799 የስልክ መስመር በመደወልና በባለስልጣኑ ማህበራዊ ሚዲያ(FDRE Education and Training Authority-ETA) ላይ እንዲሁም በዌብ ሳይት https://www.eta.et በመመልከት ህጋዊ እውቅና ስለመኖሩ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በባለስልጣኑ በኩል የተጨበርበረ የትምህርት ማስረጃ ያላቸውን ጨምሮ የሚፈለገውን መስፈረት ያላሟሉ ተቋማትን በመከታተል እውቅናቸው እንዲሰረዝ መደረጉን አስታውሰዋል።
በዚህም በአራት ወራት ብቻ ከ350 በላይ የግል የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል። በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ላይ አንዳንድ ተቋማት እጃቸው አለበት ያሉት ዶክተር አንዱዓለም ተገቢው ክትትል ከተደረገ በኋላ ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለዋል። አሁን ላይ ከህግና ስርዓት ውጭ በሚያስተምሩ ተቋማት በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ጉዳዩ ታይቶ የወደፊት እጣፋታቸውን በተመለከተም ለመንግስት እያቀረብን ነው ብለዋል። ለጊዜው ግን አንዳንዶቹን ተማሪዎች ሁኔታ በማየት እውቅና ወዳለው ተቋም ገብተው እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የመግቢያ መስፈርት ሳያሟላ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ደግሞ ጊዜያቸውና ገንዘባቸውም ከመባከኑ ውጭ ውጤት አይኖራቸውም ነው ያሉት። ህግና ስርዓትን ጠብቆ የሚያስተምሩ ተቋማትን ማበረታትና ሌሎችም ወደዚህ ስርዓት እንዲመጡ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል። አጠቃላይ ህብረተሰቡ፣ መምህራን፣ የተቆጣጣሪ ባለስልጣን፣ የወላጆችና የተማሪዎች እንዲሁም ሚዲያው በዚህ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ለትምህርት ጥራት በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሲባል በቴክኖሎጂ የታገዘ የተለየ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁንም ገልጸዋል። የተቋማትን የእውቅና እድሳትም በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ከክልልና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል። ተቋማት ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት ብቁ መምህራን፣ ቤተ ሙከራ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። የሚመዘገቡ ተማሪዎችም የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወይም ሲ ኦ ሲ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።