DW ፡ የሰሌዳ መለያ ቁጥር ኮድ 3 ያላቸው የግል የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ” ሞት ይብቃ ፣ መንግሥት የደኅንነት ከለላ ይስጠን” ሲሉ ጠየቁ። ከተለያዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ጋር በሚያደርጉት የሥራ ግንኙነት ውል መሠረት የሚሠሩት አቤቱታ አቅራቢ አሽከርካሪዎች ተሳፋሪ መስለው አገልግሎት በሚጠይቁ ወንበዴዎች እና ነፍሰ ገዳዮች በስለት ተወግተው እየተገደሉ፣ በገመድ እየታነቁ ከመገደላቸው ባለፈ ንብረታቸውም እየተዘረፈ መሆኑን ዛሬ ሰብሰብ ብለው ችግራቸውን በምሬት ገልፀዋል።
የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ማኅበር እንዳለው በአዱስ አበባ እስካሁን ስድስት አሽከርካሪዎች ተሳፋሪ ነን ብለው ጥሪ ባደረጉ አካላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። የሜትር ታክሲ አገልግሎት ማእቀፍ ዘርግተው አሽከርካሪዎችንና የ ኮድ 3 የግል አውቶሞቢሎችን አቅፈው የከተማ ውስጥ የሕዝብ ማጓጓዝ ሥራ ላይ የተሰማሩት ኩባንያዎች ለአሽከርካሪው ደኅንነት ዋስትና ሊሰጡ አልቻሉም የሚሉት አሽከርካሪዎቹ መንግሥት በሌሊት ይፈፀም የነበረው ግድያ እና የንብረት ቅሚያ በቀን ሲፈፀም በመደጋገሙ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ “መንግሥት በየ ዓመቱ ከ 450 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ገቢ የሚሰበስብበት ዘርፍ ነው” በማለት እስከ 45 ሺህ የሚደርሱ አሽከርካሪዎችን አቅፎ የያዘውን ዘርፍ በትኩረት ሊመለከተው እንደሚገባ ገልፀዋል። በኮድ ሦስት የግል አውቶሞቢል የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ ብዙዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው። ቴዲ ቡናማው ፣ አቤል አማርከኝ፣
ሳላሃዲህ ሀሰን ፣ አቶ ሀብቴ የተባሉ በእድሜ የገፉ ሰው፣ ይበልጣ እና ተወልደ የተባሉ አሽከርካሪዎች እስካሁን ተሳፋሪ ነን ብለው በተሳፈሩ ሰዎች ተገድለዋል። አሽከርካሪዎቹ ከሰሞኑ መገደሉ ሳያንስ በልፋቱና በጥረት የገዛው ተሽከርካሪ ጭምር የተዘረፈበትን ሾፌር ለማሰብ በተሰባሰቡበት ወቅት ስጋታቸውን ጭምር ገልፀዋል።
መሰል ጥቃቶች መሃል ከተማ ውስጥ ከሌሊት የጨልማ ጊዜ አልፎ በቀንም በጠራራ ፀሐይ መፈፀሙ ፍርሃት ውስጥ ከቷቸዋል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ አሽከርካሪዎቹን አቅፈው ከሚሰሩት የትራንስፖርት ኩባንያዎች መካከል ኢትዮጵያዊ ያልሆኑን ሰዎች በዚህን መሰል ወንጀል ውስጥ እየገቡ ስለሆነ መንግሥት ክትትል አድርጎ እርምት ሊወስድ ይገባል ሲሉም ተማጽነዋል። በኢትዮጵያ እየተለመዱ ከመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የሆነዉ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የመክፈል አቅም ላላቸው ሰዎች ተመራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት መሆን ከመቻል አልፈው በብዙ ሺህዎች ሰፊ የሥራ እድል እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል። ይሁን እና የአሽከርካሪዎች ካሰቡት ደርሶ በሰላም የመመለስ፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የንብረታቸው የመዘረፍ እና የተሳፋሪዎች ደህንነት ሥጋት ውስጥ እየወደቀ ይገኛል።