በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተፈጠረው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ እንዲመረመር ተመድ ጠየቀ፡፡

የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት በኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ አውጥተዋል

ድርጅቱ መንግስት ህግ የማስከበር ስራን እንዲሰራና የታገቱ ዜጎችን እንዲያስለቅቅም አሳስቧል

በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተፈጠረው ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ እንዲመረመር ተመድ ጠየቀ፡፡

ባሳለፍነው እሁድ ሰኔ 11 ቀን በኦሮሚያ ክልል ጊምቢ ወረዳ ባሉ ቀበሌዎች ማንነትን መሰረት ባደረገ ግድያ የሟቾች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱን የአይን እማ ኞች መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ኦነግ ሸኔ ፈጸመው በተባለው በዚህ ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ለመቅበር በአስከሬን ፍለጋ ላይ ጭምር መሆናቸውንና ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ ያሉ ሰዎች እንዳሉ በመጠቆም የዐይን እማኞቹ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ክስተቱን ተከትሎ በርካታ ሀገራት እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ሲሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሯ አክለውም በኦሮሚያ ክልል ማንነትን መሰረት ባደረገው ግድያ ማዘናቸውን ገልጸው መንግስት ጉዳዩን እንዲያጣራ እና እንዲመረመር ጠይቀዋል፡፡

ድርጅታቸው በአካባቢው ያሉ የአይን እማኞችን፣ከግድያ የተረፉ ሰዎችን እና ሌሎች መረጃዎችን እንደሰበሰበ የተናገሩት ኮሚሽነሯ ግድያው የተፈጸመው በጊምቢ ወረዳ ቶሌ በምትባል ቀበሌ በሚኖሩ አማራዎች ላይ መሆኑን አረጋግጠናልም ብለዋል፡፡

በግድያው ሴቶች እና ህጻናትን ዋነኛ ኢላማ እንደነበሩ፣ መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ንብረቶች ሁሉ በታጣቂዎች መውደማቸውንም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጥቃት ሳቢያም ከግድያው የተረፉ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች መኖሪያ ቀዬአቸውን ለቀው ተሰደዋል ያሉት ኮሚሽነር ባችሌት በጥቃቱ መሳቀቃቸውን እና የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን እንዲያጣራ የዜጎችን የመኖር መብት እንዲያስከብርም ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽነሯ አክለውም ታጣቂዎቹ ንጹሃንን ከመግደላቸው በተጨማሪ አግተው እንደወሰዱ ገልጸው መንግስት ህግ የማስከበር ስራውን እንዲሰራ እና የታገቱ ዜጎችን እንዲያስለቅቅ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ንጹሃን ሰለባ እየሆኑ መሆኑን የተናገረው ድርጅቱ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ሊያረጋግጥ ይገባልም ብሏል፡፡

አል-ዐይን