በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አንድ አስተዳዳሪ እና የፖሊስ ም/አዛዥ ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ታጣቂዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት እና አስተዳዳሪዎች ላይ በከፈቱት የጦር መሣሪያ ጥቃት የወረዳው አስተዳዳሪ እና የወረዳው የፖሊስ ምክትል አዛዥ መገደላቸው ተገለጠ። ግድያው ባለፈው እሑድ ሰኔ 05 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. በወረዳው ጋሌማ በተባለ ደናማ አከባቢ ጠዋት በግምት ከ3 እስከ 4 ሰዓት ገደማ መፈፀሙን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልገለጡ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ (DW) ተናግረዋል።

እንደ ነዋሪው አስተያየት፦ የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል አዛዡ ከወረዳው ከተማ ጎቤሳ የተወሰኑ የፖሊስ አባላትን አስከትለው የአርሲ ብሔራዊ መካነ-አራዊት አካል ወደ ሆነው ጋሌማ ሲያመሩ ነው ጥቃቱ በታጣቂዎች የተከፈተው። በጥቃቱም የወረዳው አስተዳዳሪ፣ የወረዳው ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል አዛዥ እና አንድ የሚሊሻ አባል መገደላቸውን ነው ነዋሪው የገለጹት።«የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል አዛዡ ባለፈው ከዚህ የሔዱት ዘመቻ ተብሎ ነው። ዝምብ ብሎ ፖሊሶች እና ቀለል ያለ ኃይል ይዘው ነው የኼዱት። ጋሌማ ውስጥ ድንኳን ተጥሏል ተብሎ ከዚህ በፊት መረጃ ደርሷቸዋል።»ነዋሪው እንዳሉት በዕለቱ ታጣቂዎች ሰዎች አግተዋል፤ የጦር መሣሪያና ገንዘብ ዘርፈዋል።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዘመዱ ኃይሉ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ እና የፖሊስ ምክትል አዛዥ በጥቃቱ መገደላቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡«በታጣቂዎች እና በሰላም አስከባሪዎች መካከል የሰው ሕይወት አልፏል። ይህ መኾኑ የታወቀ ነው። በሺርካ ወረዳ እና በሳቡሬ ድንበር ላይ ነው። ቦታው ደግሞ አስቸጋሪ ነው። የሌሎችም የወደቁ ሰዎች ሬሳ ይኖራል ብለን እናስባለን።»የአርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ ዋና ከተማ ጎቤሳ ከአዲስ አበባ 264 ኪ.ሜ ገደማ ርቀት ላይ ስትገኝ፤ ከበቆጂ ከተማ ደግሞ 35 ኪ.ሜ. ትርቃለች። ነዋሪዎቹ ከዚህ ቀደም ታጣቂዎች በአከባቢው እንደማይንቀሳቀሱና መሰል የፀጥታ ስጋትም ሲያዩ የመጀመሪያቸው መሆኑን ተናግረዋል።