ሊቢያ ኦይል ኢትዮጵያ በአዲስ ብራንድ መምጣቱን አስታወቀ

የኦላ ኤነርጂ ግሩፕ አካል የሆነው ሊቢያ ኦይል ኢትዮጵያ ሊሚትድ ከጥር 29 ቀን 2014 ጀምሮ ሥሙን በህጋዊ መንገድ በመቀየር ኦላ ኢነርጂ ኢትዮጵያ ሊሚትድ መባሉን አስታውቋል።

ኩባንያው ይህን የተናገረው በመስቀል አደባባይ የነዳጅ ማደያ እና አገልግሎት መስጫ ጣቢያው ውስጥ የሚገኘውን አክሰል አውቶ ኬር ማዕከል ባስተዋወቀበት መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት የነዳጅ ማደያ እና የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቹ በሚገነቡ የፕሪሚየም የመኪና ጥገና ማዕከላት በመታጀብ አዲሱን ብራንድ ለማስተዋወቅ በዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህንኑ የመኪና ጥገና ማዕከል እንዲያስተዳድርም ከጊጋር ትሬዲንግ እና ቴክኒካል ሴንተር ጋር የአጋርነት ሥምምነት መፈራረሙ ተገልጿል።

በአፍሪካ የኃይል አከፋፋይነት እና ግብይት ሥራ ላይ በተሰማሩ ኩባንያዎች ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነው ኦላ ኤነርጂ ግሩፕ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 አዲሱን ብራንድ በፓን አፍሪካን ኔትወርክ (የችርቻሮ መሸጫ አውታረ መረቦች) እና በነዳጅ ምርቶቹ ላይ ይፋ ማድረጉን አስታውቋል።

የኦላ ኤነርጂ ግሩፕ በደንበኞቹ ዘንድ እያደጉ ለመጡት ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ሲል በኦላ ኤነርጂ ብራንድ ሥር አዳዲስ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለማቅረብ በማሰብ ለየት ያለ የደንበኛ እንክብካቤ ላይ ትኩረት አድርጎ መምጣቱን የኦላ ኢነርጂ የችርቻሮ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት እዮኤል ቡልቲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ ዳግም ብራንድ ከተደረጉት የኦላ ኤነርጂ ግሩፕ ኔትወርክ (የችርቻሮ መሸጫ አውታረ መረቦቹ) ጋር ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ መሆኑንም እዮኤል ገልፀዋል።

አዲሱ ብራንድ በመጀመሪያ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በተመረጡ የነዳጅ ማደያና አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች የሚተገበር ሲሆን፣ በመቀጠልም በመላው አገሪቱ በሚገኙ የኩባንያው የችርቻሮ አውታሮች በሙሉ ደረጃ በደረጃ ይከናወናል ተብሏል።