የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ገለፀ።

የክልሉ ካቢኔ በዛሬው እለት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው ወቅታዊ ሁኔታዎችን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ማሳለፉን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዚሁም መሰረት የክልሉ መንግስት ካቢኔ በሰላም ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የተወያየ ሲሆን፥ በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ዙሪያ መክሯል።

በዚህም ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ እየደረሰ ያለው የሰው ህይወት መጥፋት እና የዜጎች መፈናቀል እንዲቆም ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ እና ስራ ላይ እንዲውል እንደሚሰራ አስታውቋል።

የክልሉ ህዝብ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና የሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እያቀረበ ባለው ጥያቄ መሰረትም እርምጃዎች መውሰድ መጀመራቸውን እና ይህም ተጠናክሮ የሚቀጠል መሆኑን ገልጿል።

እስካሁን በተወሰደው እርምጃም በዜጎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ ከ200 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የተቀሩትንም በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የሰላም ጉዳይ ከሁሉም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ በግጭቱ ምክንያት ችግር ያጋጠማቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመርዳት ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጿል።

በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ እንዲቆም እና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለሚሰሩ የፀጥታ ሀይሎች ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የክልሉ መንግስት ካቢኔ ያስታወቀው።

ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ እየተከናወነ ባለው ስራ ውስጥ ህብረተሰቡ ለጥፋት ሀይሎች በር ለመክፈት የሚጥሩትን በንቃት እንዲጠብቅ እና እንዲከላከለም ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም ክልሉ መንግስት ካቢኔ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን እንደ አዲስ ለመመደብ የቀረበ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ላይም ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።

FBC