ሀገር ሰላም የምታገኘው ስንት ንጹሓን ዜጎች የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ነው? – ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

May be an image of textሀገር ሰላም የምታገኘው ስንት ንጹሓን ዜጎች የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ነው ?
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ60ዎቹ ጀምሮ በተጣባት የእኛና የእነሱ የፖለቲካ ትርክት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መተኪያ የሌላቸው ውድ ልጆቿን ሕይወት ገብራለች ዛሬም ድረስ እየገበረች ትገኛለች። ሕዝባችንን የተጣባ የመገዳደል አባዜ እርስ በእርስ ተጠፋፍተን ከምድረ ገጽ እንድንጠፋ የተደረገብን ይመስል ከዕለት ዕለት ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንጓዝ የነበረውን ተስፋ እንደ ሕዝብ እያጨለመብን ይገኛል። መገዳደልን ከመለማመዳችን የተነሳ ዛሬ የት እና ስንት ሰው ተገደለ እንጂ ጎሳ ለይቶ መገዳደል ምንም የማይመስልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንደ ሀገር ክፋት እየተጣባን እኛም እየተለማመድነው እንደምንገኝ መስካሪ አያሻንም።
ባሳለፍናቸው ጥቂት ቀናት በአፋር እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎች በተላላክ እና መዲና መካከል፣ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎች በጉጂና በቡርጂ መካከል እንዲሁም በቤኒሻንጉል ክልል ካማሺ ዞን ቤሉጂጋንፎይ እና በፓዊ በተከሰተ ግጭት ብዙዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ መንግስትን አወዳሽ ሚዲያዎች “ተደመሰሰ” ቢሉንም በኹሉም አካባቢ የተዳፈነ እሳት እንጂ የጠፋ ወይም ሊያጠፋው የፈለገ እንደሌለ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የዋለ ያደረ፣ አንዳንዱም ጭሱን ዐይቶ በቀላሉ በአካባቢው ወግና ባህል መፈታት የሚችሉ ችግሮች ተጋነው ሰውን በግፍ እስከማገዳደል ደርሰዋል፡፡ እንደቤኒሻንጉል ያሉ አካባቢዎች ደግሞ በመሠረታዊነት የውጭም የውስጥም ተጻራሪ እጆች ያሉበት በመሆኑ እያንዳንዷ የምትወሰድ የመፍትሔ አማራጭ ጥንቃቄ መሻቷ አያጠያይቅም፡፡ አኹን አኹን ደግሞ ከክልሉ በአንጻራዊነት ሰላም ወደነበሩ አንዳንድ አካባቢች መዛመቱ ነገሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በተጠቀሱት ቦታዎች ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ከልብ የመነጨ ሀዘናችንን እየገለጽን ለሟች ቤተሰብ መጽናናትን እንመኛለን፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሰሚ ካለ አጥፊዎች በአስቸኳይ በሕግ እንዲጠየቁ አብክረን እንጠይቃለን፡፡
ለመጠፋፋት አዙሪቱ በዋነኛነት የእኛና የእነርሱ የፖለቲካ ትርክት ቀማሪዎችና አራማጆች፣ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ሓላፊነት የወደቀበት መንግስት የየድርሻቸውን ሓላፊነት የሚወስዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ የገባንበት የመጠፋፋት ጎዳና በዚህ ዓይነት መልኩ መቋጫ እንደማያገኝ እሙን በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፋፋዮችን፣ ጎሰኞችንና ጎጠኞችን በቃ ሊል፣ በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካና መገለጫውን፣ የእንዲህ ያለው አጀንዳ ተሸካሚዎችን ተው በቃችሁን በማለት በአንድ ድምጽ እንዲነሳ፣ ወዲህም ራሱን እያደራጀ አካባቢውን እንዲጠብቅ ፓርቲያችን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ