በሃሰተኛ ገንዘብ ነዳጅ ቀድቶ ለማምለጥ የሞከረው አሽከርካሪ ከቆመ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ህይወቱ ማለፉ ተገለፀ

በሃሰተኛ ገንዘብ ነዳጅ ቀድቶ ለማምለጥ የሞከረው አሽከርካሪ ከቆመ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ህይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የትራፊክ አደጋው የደረሰው ግንቦት 18 ቀን 2014 ከሌሊቱ 6፡30 ሰዓት ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ሚካኤል አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1- 30262 አ.አ የሆነ ተሽከርካሪ ከጀሞ 1 አቅጣጫ ወደ ሚካኤል አደባባይ እየተጓዘ 67 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ነዳጅ ሊቀዳ መግባቱን በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ቲም ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ስጦታው ወልዴ ገልፀዋል፡፡

አሽከርካሪው ነዳጅ ከቀዳ በኋላ አምስት ባለ 100 መቶ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለነዳጅ ማደያው ሠራተኛ ሰጥቶ በሚሄድበት ወቅት፤ ነዳጅ ቀጂው የብሮቹን ትክክለኛነት በመጠራጠሩ ሊያስቆመው መሞከሩን የጠቀሱት ምክትል ኢንስፔክተር ስጦታው፤ አሽከርካሪው ግን በፍጥነት በማሽከርከር ለማምለጥ ጥረት ሲያደርግ መንገድ ዳር ቆሞ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3A- 60203 አ.አ ከሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ አብረውት ተሳፍረው የነበሩ 2 ግለሰቦች ላይም ከባድ የአካል ጉዳት በመድረሱ ተጎጂዎቹ በህክምና ላይ እንደሚገኙ ምክትል ኢንስፔክተር ስጦታው ወልዴ ማስረዳታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡