አንድ ለመንገድ! – ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ከአብን

አንድ ለመንገድ!

እኔ ከሌለሁ አብን አይኖርም፣ ይዳከማል ወይም ትግሉ በሰከነ ስትራቴጅ አይመራም የሚል ግብዝነት በአንዳንድ ወንድሞች ዘንድ አያለሁ።

ወንድሜ ሆይ፦ አንተን ብቻ የአማራ ሕዝብ ሙሴ አድርጎ የፈጠረ ጌታ የለም፣ ቦታ ብንለቅላቸው ምን አልባት ከኛ በእጅጉ የተሻሉና አብንንም ሆነ የአማራን ሕዝብ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚወስዱ መሪዎች አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ።

እኛ እኮ ምንም፣ ትቢያ ነበርን። የአማራ ህዝብ ነው ከመሬት አንስቶ ለዚህ ታዋቂነትና የመሪነት ቦታ ያበቃን እንጂ ከ4 አመት በፊት ምንም ነበርን። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «እኔ ግን ትል ነኝ፣ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።» እንዳለው (መዝሙር 22፥6)

አንታበይ፣ በግብዝነት ወደ ሌሎች ጣታችን ከመጠቆማችን በፊት እኔ ማን ነበርሁ? እኔ ማን ነኝ? እንበል። ወደድንም ጠላንም አብንም ሆነ ህዝባችን አዲስ መሪ የሚፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ከቦታችን ለቀን አዲስ መሪ፣ አዲስ ፊት፣ አዲስ ተስፋ መፍጠር አለብን። በአጭር ጊዜ።

እናሸንፋለን፣ እናቸንፋለን፣ ለማሸነፍ ነው የጀመርነው ድንፋታና መፈክር የትም አያደርሰንም። ካልሆነ በታሪክና በህዝባችን ፊት ቀለን እንገኛለን።

አብን የአማራ ህዝብ መከራ አምጦ የወለደው ድርጅት ነው። መሪዎቹ እናጠፋለን እናበላሻለን፣ ለሰራነው በጎም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ስራ ሀላፊነት እንወስዳለን። ብዙ ሺህ ወጣቶች ለመተካት የተዘጋጁ ደግሞ አሉ። ለነርሱ እድል ሰጠን እኛም ማገዝ ባለብን ልክ ከኋላ ሁነን እናግዛለን። ካልሆነ እንደ አንዳንድ ብአዴናዊያን ወንበር ላይ የጎልማሳ ዕድሜ ፈጅተን፣ በስልጣን ጃጅተን የታሪክ መሳቂያ መሳለቂያ እንሆናለን።

ሌላ ስራም እኮ ሰርቶ መኖር ይቻላል!