በቡራዩና አካባቢው ሰው በመግደልና ንብረት በማውደም 38 ግለሰቦች በሽብርተኝነት ተጠረጠሩ

ከመስከረም 2 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በቡራዩ ከተማና አካባቢው በተፈጸመ ግድያ፣ የንብረት ቃጠሎና ዘረፋ ጋር በተያያዘ ታስረው ከነበሩት በርካታ ተጠርጣሪዎች ውስጥ፣ የ38 ግለሰቦች ድርጊት የሽብር ወንጀል ድርጊት ነው በመባሉ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ዓርብ ኅዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በፀረ ሽብር ሕጉ ድንጋጌ መሠረት 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ የፈቀደባቸው ተጠርጣሪዎች፣ በቡራዩ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ የከረመና ፈጽመውታል የተባለው ድርጊት የሽብር ድርጊት መሆኑን በምርመራ የተገኙ ማስረጃዎች አመላካች ሆነው በመገኘታቸው ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤት የተዛወሩ ናቸው፡፡ በተጠረጠሩበት የግድያ፣ የንብረት ቃጠሎና ዘረፋ፣ እንዲሁም ከባድና ቀላል የአካል ማጉደል ወንጀል ምርመራ እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ 28 ቀናት እንዲፈቀድለት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከሁለት ወራት በላይ በቡራዩ ወረዳ ፍርድ ቤት መታሰራቸውን በመግለጽ፣ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በማጠናቀቁ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ፖሊስ የጠየቀውን 28 ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ከመስከረም 5 እስከ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በተፈጠረ ብጥብጥ ሰው በመግደል፣ አካል በማጉደልና ንብረት በማውደም በተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ላይ ዓቃቤ ሕግ በአሥር ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሠርት ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ላለፉት ሁለት ወራት በ14 ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያጣራ የቆየውን የምርመራ ሒደት ማጠናቀቁንና ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን የፌዴራል ፖሊስ በማሳወቁ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠረት አሥር ቀናት ፈቅዷል፡፡

በቡራዩና አካባቢው፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች በተቀሰቀሰ ረብሻና ብጥብጥ የ30 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡