“የኢትዮጵያ መንግስት የታሰሩትን ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰራተኞች በአስቸኳይ መልቀቅ አለበት”:-ሲፒጄ

አለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተማጓች ኮሚቴ “ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ” (ሲፒጄ) የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የታሰሩትን 11 ጋዜጠኞችና እና የሚዲያ ሰራተኞች በአስቸኳይ መልቀቅ አለበት ብሏል፡፡

ኮሚቴው መንግስት ባለስልጣናት በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ የሚያደርጉትን ማስፈራሪት ያስቁም ሲልም ጠይቋል፡፡

ሲፒጄ የአማራ ክልል መንግስት እያካሄደ ባለው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ከግንቦት 11 ጀምሮ በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ 11 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለሙያዎች መያዛቸውን ባውጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡

በክልሉ በህገወጥ እንቅስቃሴ ተጠርጥረው 4500 ሰዎች መያዛቸውንም ጨምሮ ጠቅሷል፡፡

“የታሰሩት ንብረትነቱ የግል የሆነው የአሻራ የዩቱዩብ አምስት ጋዜጠኞች፣ የንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 4 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የንቃት ሚዲያ መስራች እና ኤዲተር መስከረም አበራ እንዲሁም የገበያኑ ሚዲያ መስራችና ባለቤት ሰለሞን ሹምየ” መሆናቸውን ሪፖርቱ ዘርዝሯል፡፡

የሲፒጄ የአፍሪካ ተወካይ እርምጃው መንግስት ለፕሬስ ነጻነት እና ለዜጎች መረጃ የማግኘት መብት ክብር እንደሌላው ያሳያል ብለዋል፡፡ ሲፒጄ በአማራ ክልል ተካሂዷል ካለው እስር በተጨማሪ የኦሮሚያ ኒውስ ኔትወርክ ጋዜጠኞች ደሱ ዱላ እና ቢቂላ አሜኑ በአስቸኳይ እንዲፈቱ መጠየቁንም አል ዐይን አማርኛ ዘግቧል፡፡

ከህወሓት ሊሰነዘር ይችላል ያለውን ጥቃት ለመመከት የክልሉን የውስጥ ሰላም በማስፈን አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ያለው የክልሉ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚቀጥልበት እየገለጸ ይገኛል፡፡

የአማራ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ የክልሉን ከትናንት በስትያ “በህግ ማስከበር ዘመቻ”ው ከ4500 በላይ ግለሰቦች መያዛቸውን ማስታወቁም ይታወሳል፡፡

የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የህግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኃላፊው፤ እርምጃ እየተወሰደ ያለው በፋኖ ሥም ተደራጅው በህገወጥ ድርጊት በሚሳትፉት ላይ ነው ብለዋል፡፡