ከብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

ከብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው፤ ሕገ-ወጦችን ወደሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሒደት ላይ ትገኛለች።

ለውጡ በሕዝባችን ትግልና ግፊት የመጣና ሃገራችንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግር፣ ለሃገራችን ዘላቂ ብልጽግና መሠረት የሚጥልና የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩበት የመንግሥት አስተዳደር ለመዘርጋት የሚያስችል ነው።

ለውጡን ተቋማዊና ዘላቂ ለማድረግ መንግሥት የተቋማት፣ የሕግ እና የፖሊሲ ማሻሻያ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የሕዝብ አመኔታና ቅቡልነት ያላቸው ተቋማትን ለመገንባት ተዓማኒነትና ተገቢ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ከመሾም ጀምሮ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች ተጀምረዋል።

በዚህ ሕዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጥቅማቸው የተነካ የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝባዊውን የለውጥ ሒደት ለማደናቀፍ፣ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረው አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና የመረዳዳት ባሕል ተሸርሽሮ በምትኩ ቂምና ቁርሾ እንዲኖር፣ በበሂደትም ግጭት ተስፋፍቶ ሞት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ሰብዓዊ ቀውሶችን በማስፋፋት ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደተባለው ለዉጡን በመቀልበስ ለሌብነት፣ ለዝርፊያ እና ሰብዓዊ መብቶችን እንዳሻቸዉው እየጣሱ ያለተጠያቂነት መኖር የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

መንግሥት ህግን በማስከበር በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በሃገር ሀብት ዝርፊያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ አቅጣጫ ለማሳት እና ለመቀልበስ ሲረባረቡ ይስተዋላል።

እነዚህ ኃይሎች የተጀመረውን ለውጥ በማደናቀፍ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ
ሲሉ የብዙ ንጹሃን ዜጎችን ሰላምና እንዲሁም የሀገራችንን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል በመንቀሳቀስ ይገኛሉ።

በዚህም ምክንያት ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አቅደው ግጭቶችን በመቀስቀስ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል፣ ብዙዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ይህንን ችግር በመቅረፍና ለግጭቶቹ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ወደሕግ ለማምጣት በችግርና በእንግልት ላይ ላሉ ዜጎችም ድጋፍ ለማድረግ መንግስት ህዝቡን በማስተባበር ሰፊ ርብርብ ሲያደርጉ እንደቆየ ይታወቃል።

ሆኖም ግን እነዚህ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እየታዩ በመሆናቸው የተጠናከረ ምላሽን የሚጠይቁ ሆነው ተገኝተዋል።

የመንግሥት ቀዳሚ ግዴታ የሕዝባችንን ደኅንነት መጠበቅና የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ነው።

በመሆኑም የኢፌዴሪ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በቅርቡ በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እና ሰብዓዊ ቀውስ አስመልክቶ ዛሬ ሕዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በጥልቀት መክሯል።

ምክር ቤቱ በአካባቢው የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ጉዳቱን በጥልቀት በመገምገም ከክልሎቹ መንግሥታት ጋር ባደረገው ውይይት የአካባቢውን ሰላም የማስከበር፣ የዜጎችን ህይወት የመታደግ እና በአካባቢው የህግ የበላይነትን በማስከበር አስተማማኝ ሰላም እና ጸጥታን የማስፈን ጉዳይ ከሁለቱ ክልሎች አቅም በላይ መሆኑን እና የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት ጣልቃ ገብተው ችግሩን እንዲያረጋጉ ክልሎቹ በጠየቁት መሰረት የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በአካባቢው ተሰማርተው የህግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ፣ የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ወደ ቤትና ንብረታቸው መልሶ በማቋቋምና ሰላም እንዲያሰፍኑ ወስኗል።

በመሆኑም በአካባቢው የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ ይሠራሉ፤ በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ የሚያቀርቡም ይሆናል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትንና የሕዝባችንን ደኅንነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነቱን ይወጣል።

እንዲሁም ይህ እርምጃ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ሕልም ዕውን የሚሆነው ሕግና ሥርዓት ሲኖር ነው።

ሕገ-ወጥነትና ሥርዓተ-አልበኝነት ባለበት ሃገር ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ዕድገት ከቶ ሊታሰብ አይቻልም።

በመሆኑም የፌደራልና የክልል መንግሥታት አካላት የሕዝብና የሃገር ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ለውጡን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚናውን ሲወጣ እንደቆየው አሁንም አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌዴሪ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE