የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ስለተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የቀረበው ሪፖርት እንዳስደነገጠው ገልጿል ።

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ስለተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የቀረበው ሪፖርት እንዳስደነገጠው ገልጿል ።

የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ መብት ልዩ መልዕክተኛ ኤሞን ጊልሞር በትናንትናው ዕለት ለሶስት ቀናት ከተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ስላደረጉት ውይይት ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥተዋል ። በመግለጫውም ከሰብዓዊ መብት ጥሰት አንፃር የቀረበው ሪፖርት እንዳስደነገጣቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ። በኢትዮጵያ በነበራቸው የሶስት ቀን የስራ ውይይት በትኩረት ለማየት የሞከሩት ከሰብአዊ መብት ጋር ተያይዞ ሶስት ጉዳዮችን እንደነበር አንስተዋል ።

እነርሱም የሰብአዊ እርዳታ ሁኔታ፣ አገራዊ የምክክር ሂደት እና የሰብዓዊ መብቶች እና ተጠያቂነት እንደነበሩ አብራርተዋል ። ከሰብአዊ እርዳታ አንፃር ብዙ አስቸጋሪ እና ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች እንዳሉ ያነሱት ልዩ መልዕክተኛው የአስተዳደር ችግር ፣ ቴክኒካል ጉዳዮች እና የተቀሩት ደግሞ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረሻ መንገዶች መሆናቸውን ገልጸዋል ።

ይህንንም ችግር ከተለያዩ የመንግስት ተወካዮች ጋር እንደተወያዩበት እና መልዕክቱም በሚገባ ለመንግስት ደርሷል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀው ፣ ችግሩ ተፈትቶ በተስተካከለ መልኩ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከድርቁ እንዲሁም አሁን በሀገራችን ላለው አስፈላጊ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚደርሱም አክለዋል ። ከአገራዊ ምክክር አንፃርም እንደ አውሮፓ ህብረት በኦባሳንጆ ሲደረግ የነበረውን ዘላቂ ሰላም የማምጣት ሂደት በእጅጉ እንደሚደግፉ ገልፀዋል። በተጨማሪም አሁን በጅምር ላይ ያለው አገራዊ የምክክር ሂደት ሁሉን አካታች መሆኑ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል ።

“ከእራሴ ልምድ እና ከሌሎችም እንዳየሁት ሴቶችን የምክክር ሂደት ውስጥ ማስገባቱ እጅግ ወሳኝ ነው” ሲሉ ያክላሉ ። ሶስተኛው እና የመጨረሻው ጉዳይ የነበረው ከሰብአዊ መብቶች እና ተጠያቂነት አንፃር የተደረገው ውይይት መሆኑን ያነሱት ልዩ መልዕክተኛው ፤ በቀረበው ከአንድ አመት ከግማሽ በላይ በነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት በእጅጉ መደንገጣቸውን ገልፀዋል ። በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሀየር ኮሚሽን ፎር ሂዩማን ራይትስ በጋራ ያወጡትን ሪፓርት መመልከታቸውን የገለፁት ኤሞን ጊልሞር አጥፊዎቹ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል ።

መቼ፣የት፣ማን አደረጋቸው የሚሉትን ትተን እዚህ የተመለከትነው ጉዳይ ከፍርድ ውጭ የሆነ ግድያ እና አሰቃቂ የሆነ ፆታ ተኮር ጥቃቶችን ነው፣ ይህም በእኛ ዘንድ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል ። በዚህም መሰረት ገለልተኛ የሆነ ኮሚቴ ተቋቁሞ በጥምር የተሰራውን የምርመራ ስራ እንዲገመግም ሀሳብ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል ።