“የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ህልማቸው ወደ መቃብር ይወርዳል” – ኦዴፓ (የቀድሞ ኦሕዴድ

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዲፒ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዛሬው እለት ስብሰባውን አካሂዷል።

ማእከላዊ ኮሚቴው በስብሰባው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ትግሉ ከየት ወዴት እየተጓዘ ነው፣ በእጃችን ላይ ምን አለ፣ ምን አገኘን፣ ምን ይቀረናል፣ አሁን የተገኙትን እንዴት አገኘን፤ ምን ከሆነ ከእጃችን ሊወጣ ይችላል፤ የተገኘውን ድል እንዴት መጠበቅ ይቻላል በሚሉ እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አስታውቋል።

ማእከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫም ከመራራ እና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ አሁን በሀገሪቱ መታየት የጀመረውን የተስፋ ብርሃን ስልጣን ያለአግባብ ሲጠቀሙ የነበሩ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዝርፊያ ሲያካሂዱ የነበሩና ይህ ጥቅማቸው ከእጃቸው የወጣ አካላት ትግሉን ወደ ኋላ ለመመለስ በሁሉም ስፍራዎች ግጭቶች እንዲከሰቱ በማድረግ በሰው ልጅ ላይ መፈፀም የሌለባቸው አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈፀሙ በማድረግ እና ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየሰሩ ነው ብሏል።

ይህ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ህልማቸው ወደ መቃብር ይወርዳል እንጂ መቼም ቢሆን የኦሮሚያ ክልልን የብጥብጥ እና የጦርነት አውድማ አያደርጋትም ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

እርምጃችን በግልፅ የሚታወቅ ነው ያለው ፓርቲው፥ ባርነትን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንዲሁም የተደራጀ ሌብነትን ከስሩ ነቅሎ ለመጣልና በዜጎች ላይ አሰቃቂ ተግባራትን ሲፈፅም የነበረ እጅ እንዲሰበሰብ ብቻ ሳይሆን ለሰራው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆን በእጃቸው ካቴና በማስገባት ህግ ፊት ማቆም ጀምረናል ብሏል።

ፓርቲው እነዚህ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት እነዚህ አካላት የሰሩት ጥፋት እንዲደበቅ አሊያም ህግን ለማስከበር የተጀመረው ስራ እንዲቋረጥ ለማድረግ በአጠቃላይ ወደ ነፃነት የተጀመረው ጉዞ እንዲደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን አስታውቋል።

እነዚህ የተደራጁ ሌቦች በሚሸርቡት ሴራ የኦሮሞን ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ለማጋጨት ሲሞክሩ እቅዳቸው ሲከሽፍ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ለማጋጨት እየሰሩ እንደሚገኙም ፓርቲው ገልጿል።

ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሰላም የሚኖሩ ኦሮሞዎችን፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ወሰን አካባቢ በሞያሌ፣ በጭናክሰን እና ባቢሌ ወረዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ህዝቦች ላይ አሰቃቂ የሆነ ግድያ እንዲሁም ከቤት ንብረት የማፈናቀል ወንጀል እየፈፀሙ ነው ብሏል።

እንዲሁም የተደራጀ ጦርነት በመክፈት በሰላማዊ ህዝብ እንዲሁም የህዝብ ጋሻ በሆነው እና በህዝቡ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ከፊት ሆኖ የሚከላከለው የኦሮሚያ ፖሊስ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል።

የዚህ የተደራጀ ወንጀል አላማም በጥቅሉ ሲታይ የኦሮሞ ልጆችን ደም በማፍሰስ ኦሮሚያን የጦር አውድማ በማድረግ አንድነታችንን በማፍረስ፤ በህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርገው ህዝብን ሀብት ለመዝረፍ እንዲሁም ህዝቡ ወደ ነፃነት የሚያደርገው ጉዞ እንዲደናቀፍ በማድረግ ለሌብነት፣ ለዝርፊያ እና የባርነት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው ብሏል።

በክልሉ ህዝብ እና በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ላይ እየተፈፀመ ላለው አሰቃቂ ወንጀል የተሰማውን ሀዘን የገለፀው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ በአሁኑ ወቅት በዘራፊዎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ መውሰድ የተጀመረው እርምጃ መቼም ቢሆን ወደ ኋላ እንደማይመልስ አስታውቋል።

አሁን የተገኘው ለውጥ በነፃ አልተገኘም፤ በደም እና በከፍተኛ መስዋእትነት ነው ያለው ፓርቲው፥ የኦሮሞ ህዝብ አሁንም ቢሆን በተለያዩ አካባቢዎች እየከፈለ ያለው መስዋእትነት ድላችንን የሚያጠናክር እንዲሁም እልህ ፈጥሮብን ወደ ነፃነት የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን እንጂ መቼም ቢሆን ወደኋላ አይመልሰንም ብሏል።

ፓርቲው አያይዞም ሰሞኑን ለተሰዉ ሰላማዊ ዜጎች እና የፀጥታ አካላት ያለውን አክብሮት በመግለጽ፤ ለተሰዉ ዜጎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መፅናናትን ተመኝቷል።

ምንም ያክል ችግር ውስጥ ብንሆን እና በተለያየ መንገድ ቀዳዳ በመክፈት ጥቃት እየፈፀሙ ሊያዘናጉን ቢሞክሩም፤ የህዝቡን ፍላጎትና ጥቅም ለማረጋገጥ ለመስዋእትነት የተዘጋጀን በመሆኑ ለአፍታም አንዘናጋም ብሏል ፓርቲው።

በህዝባችን ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላትንም የገቡበት ጉድጓድ በመግባት ለህግ በማቅረብ ተመልሰው ጉዳት ማድረስ እንዳይችሉ እንሰብራቸዋለንም ብሏል።

በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው የሞት እና የመፈናቀል አደጋ በአፋጣኝ ቆሞ ህዝቡ ያለስጋት እንዲኖር ከክልሉ ህዝብ ጋር በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው ፓርቲው ያስታወቀው።

ከዚህ በመነሳትም የክልሉን ሰላም በቅርብ ቀናት ውስጥ በማረጋገጥ ህዝቡን ከሰቀቀን እንደምንገላግል ምንም ጥርጥር የለንም ብሏል ፓርቲው።

አሁን የተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ከአፈ ሙዝ ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ትግል እንዲካሄድ ስራ ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ነው ያለው ፓርቲው።

በሰላማዊ መንገድ መታገል ከሚፈልጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ
ለመስራት እንዲሁም የፓርቲያቸው ፕሮግራም ከኦዲፒ ጋር ተመሳሳይ ከሆነ እና ለመዋሃድ ፍቃደኛ ከሆኑት ጋር ውህደት ለመፍጠር ፍላጎታችን ከፍተኛ ነው ብሏል።

ፕሮግራማችን እና መስመራችን ከማይቀራረብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም የሀገሪቱን ህግ መንግስት እስካከበሩ እና ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እስከሰሩ ድረስ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።

በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከውጭ ሀገራት የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ስምምነታቸውን እንዲያከብሩ እና የሀገሪቱን ህገ መንግስት በማክበር ለህግ የበላይነት መከበር እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርቧል።

የኦዲፒ ማእከላዊ ኮሚቴ በኢኮኖሚ የተደገፈ ፖለቲካን ለመፍጠር እና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኦሮሚያ ክልል የኢኮኖሚ አብዮት ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኦኮኖሚ ምንጮችን ማስፋፋት፣ ለፋብሪካዎች የገበያ ትስስር መፍጠር፣ ለወጣቶች በስፋት የስራ አድል መፍጠር እና በአርሶ አደሩ ምርት ላይ እሴት በመጨመር የህብረተሰቡን ትስስር ማጠናከር ላይ በትኩርት እንደሚሰራም አስታውቋል።

የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሰረቱ ተቀርፎ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል የተተበተበ አሰራርን የሚያስቀር የመንግስት መስሪያ ቤቶች ማሻሻያ ከቀበሌ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሲቪል ሰርቪስ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጿል።

መደማመጥ፣ መረዳዳት እና መደጋገፍ ካለ አሁን ያደረገነው ትንሽዬ እንቀስቃሴ አንድ ታኮ ወደ ፊት እንድንራመድ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ወደሆነው ግብ የማንደርስበት ምክንያት የለም ብሏል ፓርቲው።

ስለዚህ አሁን እየታዩ ያሉ የለውጥ ድሎች እንዲቀጥሉ የሰፊው ህብረተስብ ድጋፍ ወሳኝ ነው ያለው ፓርቲው፥ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶች እና የኦሮሞ ወጣቶች አሁን የተደረሰበት የትግል ምእራፍ በግማሽ መንገድ ላይ ስለሚገኝ አንድነታችንን ካጠናከርን ወደኋላ መመለስ ወደማይችል እድገት እና ለውጥ እንሸጋገራለን ብሏል።

ስለዚህ ለውጥ ለማምጣት በችግር ወቅት አብረን እንደቆምን ሁሉ በዚህ በሽግግር ወቅት አብሮ በመቆም ወደ ሙሉ የነፃነት ብርሃን በጋራ እንሸጋገር ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

Via FBC