ዜጎች ወጥቶ መግባትም ሆነ አምሮቶ ለመለወጥ ብሎም ህይወታቸውን ለማስቀጠል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ተባለ

በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች የመድረክ መግለጫ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በመግለጫው ባሁን ወቅት በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች ሰላም በመራቁ ሰላማዊ ዜጎች ወጥቶ መግባትም ሆነ አምሮቶ ለመለወጥ ብሎም ህይወታቸውን ለማስቀጠል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ያትታል፡፡ የመድረክ ዋና ፀሃፊ አቶ ደስታ ዲንቃ በተለይም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ መንግስት የዜጎችን ፀጥታ ለማስከበር እወስዳለሁ በሚላቸው እርምጃዎች ተጠያቂነትን የሚያስፍን አካሄድ መከተል ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡

በአገሪቱ ሁሉም አቅጣጫዎች ለሚከሰቱ ችግሮች መንስኤው የፖለቲካ ችግር ነው ያለው መድረክ መፍትሄውም በዚህ ላይ መስራት ነው ብሏል፡፡ ዋና ጻሃፊው አቶ ደስታም በተለይም በቅርብ ጊዜያት በኦሮሚያ መንግስት በታጣቂዎች ላይ እርምጃ ሲወስድ ለሰላማዊ ዜጎች የሚያደርገው ከለላ በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሃላፊው አክለውም የኢትዮጵያ ሌላው ችግር ሆኖ ሰሞኑን ብቅ ያለው የሃይማኖት ግጭት የሚመስል አካሄድ በራሱ ፈተናውን እንደመኪያከብ አብራርተዋል፡፡ መፍትሄውም መንግስት ችግር በሚኖርበት ጊዜ ፀጥታን ከማስከበር ውጭ በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ የአለመግባት መርህን በማክበር ችግሩ እልባት ሊያገኝ ይገባል ነው ያሉት፡፡

መድረክ በመግለጫው በትግራይ እየተስተዋለ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እና የእርዳታ ፍላጎት ምላሽ እንዲያገኝ በአጽእኖት ሊሰራበት ይገባል ይላል፡፡ እንደ አገር ያለውን ችግር በዘለቄታው ለመፍታትም መንግስትን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ያሉ ተፋላሚ ኃይላት ከጦርነት ይልቅ የሰላም መፍትሄ መፈለግ አለባቸውም ይላል፡፡

ከቀናት በፊት ከዶይቼ ቬለ ጋር ቃለመጠይቅ ደረጉት የፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ መንግስት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በሚወስዳቸው ወታደራዊ እርምጃዎች ንጹሃንን ያልለየ አካሄድ ይከተላል በሚል በመንገስት ተቀናቃኞች የሚቀርበውን ነቀፋ አጣጥለው፤ መንግስት ለሰላማዊ ዜጎች ከለላ እንደሚያደርግ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡