ሕግ ማስከበርም ሆነ ማክበር አለመቻል አደጋ ደቅኗል

የሕግ የበላይነትን የ11ኛ ክፍል የሲቪክ ትምህርት ምዕራፍ ሁለት በሚከተለው መንገድ ይተነትነዋል፡፡ ‹‹Rule of law means that all citizens are subject to the law and equal under the law. Law is supreme in the country. No person or government organ is above the law.›› ወደ አማርኛ ሲመለስ፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ማለት ሁሉም ዜጋ ከሕግ በላይ አይደለም፣ እንዲሁም በሕግ ፊት እኩል ነው ማለት ሲሆን፣ ሕግ በአንድ አገር ውስጥ ፍፁም የበላይ መሆኑን ያመላክታል፡፡ በሕግ የበላይነት መርሕ መሠረት በአንድ አገር ውስጥ ማንም ዜጋም ሆነ የመንግሥት ተቋም ከሕግ በላይ አይደለም፤›› ተብሎ መተርጎም ይችላል፡፡

በተለያዩ የሕግና የፖለቲካ ትንተናዎች የሕግ የበላይነት ጽንሰ ሐሳብ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቶት ይገኛል፡፡ የሕግ የበላይነት (Rule of Law) ከዴሞክራሲ መርሆዎች አንዱ ነው ተብሎም ይታሰባል፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የብዙኃን የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብት፣ እኩልነት፣ ወዘተ እየተባሉ ከሚዘረዘሩ የዴሞክራሲ መርሆዎች አንዱ የሕግ የበላይነት መሆኑን ከበርካታ መዛግብት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ፣ ወንጀልና ሕግ አከባበር በ11ኛ ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ክፍሎች በሲቪክስና በሌሎች ትምህርት ምዕራፎች ላይ ተደጋግመው የሚሰጡ መሠረታዊ የሕግ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ በሥነ ሕግ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ወደ ላይም ሆነ ወደ ታች ባሉ የትምህርት እርከኖች ይነስም ይብዛ እነዚህን መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች ትውልዱ በትምህርት እየቀሰመ የሚያድግበት ዕድል መኖሩን ከዚህ ሁኔታ መገመት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ የነቃ የሕግ ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው ተብሎ በሚገመትባት ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት ሕግ ማስከበር ከባድ አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ የፍትሕ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል መሐመድ፣ ችግሩ ከግንዛቤ ብቻ እንደማይመነጭ ነው የሚያስረዱት፡፡

‹‹የወንጀል መከላከል ሥራው ላይ ካሉን ሚናዎች አንዱ የወንጀል መከላከል ንቃት (ግንዛቤ) መፍጠር ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የወንጀል ግንዛቤ ወይም ንቃተ ህሊና ጉድለት ችግር ሳይሆን፣ ሆን ብሎ ሕግን የመጣስ ችግር ነው የጎላው፡፡ ወንጀሎች ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት በሚገባ ዝግጅትና ቅስቀሳ እየተደረገ፣ እንዲሁም የሆነ ዓላማን ለማሳካት በማቀድ እየሆነ ነው፡፡ በየሚዲያው ሰዎችን ቀስቅሶና ልኮ የሚያስገድለው ሰው ይቅርና ታዳጊ የሚባል የስምንተኛ ክፍል ልጅም ሰውን መግደል ወንጀል እንደሆነ በደንብ ያውቃል፡፡ ሰዎችን ማፈናቀል ወንጀል መሆኑን ማንም ያውቃል፡፡ በቤተሰቡ ወይ በራሱ እንዲሆን የማይፈልገው ነገር በሌሎች ላይ ሲፈጸም ሁሉም ሊያመው መቻል አለበት፤›› ሲሉ ነው አቶ አወል የችግሩን ምንጭ የሚያስረዱት፡፡

ኃላፊው ሐሳባቸውን ሲያክሉም የሕግ ትምህርት መስጠት አለመስጠት ችግር ሆኖ እንደማያውቅ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹አብዛኛውን ችግራችን የዕውቀት ወይ የግንዛቤ ማነስ አይደለም፡፡ እኔ እዚህ ተቋም ከገባሁ ጀምሮ ተከታታይ የወንጀል ንቃት ትምህርቶች ሲሰጡ አውቃለሁ፡፡ የግንዛቤ ወይ የዕውቀት ሳይሆን ሆን ብሎ ግብ አስቀምጦ ለሆነ ፍላጎት ወይ ውጤት ወንጀል መሥራት ነው ችግራችን፡፡ የጥላቻ ንግግሮች ወንጀል መሆናቸውን፣ የጦርነት ቅስቀሳ ንግግሮች የሕግ ጥሰት መሆናቸውን ሁሉም ያውቃል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ግንዛቤ ትምህርቶችን መስጠት እንዳለበት ይታመናል፡፡ ነገር ግን ሆን ተብሎ ግደል ይህን አውድም የሚሉ ቅስቀሳዎችና ዓላማ ያነገቡ የተደራጁ ወንጀሎችን በዚያው ልክ ማስቆምም አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፤›› በማለትም ጉዳዩ ተደራጅቶ ሕግን የመጣስ እንደሆነ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ አስቀምጠውታል፡፡

በኢትዮጵያ ይብዛም ይነስ ወጣቶች የሕግ የበላይነትን መሠረታዊ ዕውቀት የጨበጠ ትውልድ ሆነው የሚያድጉበት ዕድል ቢኖርም፣ ነገር ግን በዋናነት በወጣቱ ዘንድ የተባባሰ የሕግ ጥሰት ሲፈጸም ይታያል፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች የሕግ የበላይነት መርህ መሸርሸሩን አመላካች ሆነው ይቀርባሉ፡፡ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው ቀውሱን የፈጠረው  የሕግ የበላይነት ግንዛቤ ማጠር ሳይሆን፣ ሕግን የማስከበር ሥልጣን የተሰጠው አካል ኃላፊነቱን ተገንዝቦ በተገቢው ሁኔታ አለመወጣቱ ነው ይላሉ፡፡

ይህን ሐሳብ ከሚጋሩት አንዱ የሆኑት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ አሰፋ፣ የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ በተጨባጭ በተግባር የተተረጎመበት ጊዜ አለ ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ሳይሆን የባለሥልጣናት የበላይነት ነው በኢትዮጵያ ያለው ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እጅግ ተባብሶ አገሪቱን አደጋ ላይ እንደጣላት ነው የሚያስረዱት፡፡

‹‹የሕግ የበላይነት የሕግ ተፈጻሚነትን ኃይል/ደረጃ የሚያመላክት ነው፡፡ ሕጉ በትክክል በተግባር ተፈጻሚ ሲሆን ነው የሕግ የበላይነት አለ የምንለው፡፡ በእኛ አገር መንግሥታት ታሪክ ግን ሕግ ሳይሆን ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ናቸው የሕጉም የበላይ ሆነው የምናገኛቸው፡፡ በንጉሡ ጊዜ ንጉሡ፣ በደርግ ጊዜ ደርግ፣ በኢሕአዴግም ጊዜ ኢሕአዴግ ነበሩ የበላዮች እንጂ ሕጉ አልነበረም፡፡

‹‹እኛ አገር ያለው የሕግ የበላይነት ሳይሆን የሰዎች ከሕግ በላይ የመሆን ነው፡፡ ግለሰቦች፣ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች፣ የጎበዝ አለቆች የፈለጋቸውን የሚያደርጉበት ሥርዓት ነው የተፈጠረው፡፡ በዘር፣ በቀዬና በሃይማኖት ቡድን ፈጥረው የፈለጉትን የሚያደርጉ ኃይሎች ተበራክተዋል፡፡

‹‹ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የመንግሥት ቀዳሚው ሥራና ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ነገር በሙሉ ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና ለደኅንነታቸው እንዳይሠጉ ማድረግ ነው የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ፡፡ እነ እከሌ ናቸው የችግሩ ምንጭ እያሉ ሰበብ መፍጠር አይሠራም፡፡ የሕግ የበላይነት ባለመከበሩ ምን ያላጣነው ነገር አለ? ንብረታችንን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ሁሉ እያጣን ነው፡፡ ከተማ ውስጥ እየኖርን እንኳ ከሥጋት አልወጣንም፡፡ ደኅንነታችንም ሆነ ሕይወታችን ተናግቷል፤›› በማለት የተናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ፣ የሕግ የበላይነት በተግባር ባለመተርጎሙ ያለውን ከባድ አደጋ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በወጣቱ በኩል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ የሕግ ጥሰት መስፋቱ ጎልቶ ይተቻል፡፡ ከፖለቲከኞች እስከ ምሁራን፣ ከሕግ አስከባሪዎች እስከ አገልግሎት ሰጪዎች፣ በሁሉም ዘርፍ የሚፈጠረው የሕግ ጥሰት የሕግ የበላይነትን በተጨባጭ ለመተርጎም ፈተና መሆኑን ብዙዎች ያስቀምጡታል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በቶሎና በጊዜ መቀጨት ባለመቻሉ እየተባባሰ መጥቶ፣ ዛሬ የሕግና ሥርዓት መሠረት በሆኑ የእምነት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር መግባቱ ይነገርለታል፡፡

የሕግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻሉ ኢትዮጵያውያን ለረዥም ዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የሃይማኖት መከባበርና መቻቻል ቀስ በቀስ ሸርሽሮ ወደ እምነት ግጭት ያዘነበሉ ያልተለመዱ ቀውሶችን በመካከላቸው እየፈጠረ መሆኑን ነው ብዙዎች በሥጋት የሚናገሩት፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ገና በጊዜ ሲያቆጠቁጥ ባለመቀጨቱና በማድበስበስ በመታለፉ፣ ዛሬ አድጎ የአገር ምሰሶ የሆኑ የእምነት ተቋማትን አናግቷል የሚለው ሐሳብ እየጎላ ነው፡፡

ይህን የሚስማሙበት የፍትሕ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አወል፣ ‹‹በፊት በዘር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በሃይማኖት እየተሞከረ ነው፡፡ ሆን ብለው በጅተውና አቅደው ይህን መሰል ወንጀል ለመፈጸም የተደራጁ ኃይሎች እዚህም እዚያም አሉ፡፡ ይህን ማስቆም ደግሞ ዋናው የፀጥታ ኃይሎች ሥራ ነው፡፡ የደኅንነት መዋቅሩ የት ቦታና በእነ ማን ወንጀሎቹ ይፈጸማሉ የሚለውን በጥልቀት አጥንቶ ዕርምጃ ይውሰድ፡፡ ያ ሲሆን እኛም ፋታ አግኝተን ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ላይ እናተኩራለን ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ ችግሩ የደረሰበትን ደረጃና መፍትሔውን አያይዘው ያስረዳሉ፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ አልቻለም የሚል ትችት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከብዙ ወገኖች ይደመጣል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) በጥር ወር በመቶ ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ከካቢኔ አባላት ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ደካማነት በጉልህ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹በብዙ ማስረጃዎች ልከራከራችሁ እችላለሁ እኛ ስለፍትሕ ለማውራት ብዙ ሩቅ ነን፡፡ ስለፍትሕ ለማውራት አንችልም፤›› ብለው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ከፖሊስ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ዕርከኖች በገንዘብ የሚደለልና ተገቢ ፍትሕ የማይገኝበት መሆኑን በሰፊው ተችተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ክልል ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ባሉ ጊዜያት፣ በትግራይ ተወላጆች አያያዝና ፍትሕ አሰጣጥ ላይ ታይቷል ያሉትን ጉድለት ነበር እንደ አንድ ማሳያ አድርገው ያቀረቡት፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አወል ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች ሰፊ መሆናቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ሲባል ብዙ ጊዜ ከስሙ ነው መሰል የመብራት፣ የውኃና ሌላም የማኅበራዊ ፍትሕ አገልግሎት ተጓደለብኝ የሚል ቅሬታ ሁሉ ነው የሚቀርብልን፡፡ ነገር ግን እኛ በቀጥታ የሚመለከተን የራሳችን ኃላፊነት አለብን፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋናው ደግሞ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ወይም ከሰላም ጋር የሚገናኘው የፍትሕ ሥራ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ደግሞ እኛ በዋናነት የምንጫወተው ሚና የወንጀል ምርመራ ሥራን መምራት፣ ምርመራው ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ይሆናል፡፡ የተመረመረው ወንጀል ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ አጥፊዎች እንዲጠየቁ ማድረግም የእኛ ሥራ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ የወንጀል መከላከል ሥራዎችም ሆነ ሌሎች ሚናዎች የእኛ ኃላፊነት አይደሉም፡፡ እኛ ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ እንጂ ከመፈጸሙ በፊት ያለው ሥራ አይመለከተንም፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ነው ይህ ኃላፊነት ያለበት፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ትልቅ ችግር ግን ወንጀል መከላከል ላይ ሥራ አልተሠራም የሚል ነው፡፡ የፀጥታ ተቋማትና ፖሊስ ወንጀል ሊፈጸሙ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች ቀድመው መርምረው ማስቆም እንዳለባቸው ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወንጀል እዚህ ቦታ ሊከሰት ነው ብሎ ማስጠንቀቅም ሆነ ወንጀሉን ላስቁም ብሎ የፍትሕ ሚኒስቴር ቢንቀሳቀስ፣ በሌሎቹ የፍትሕ ተቋማት ላይ ጣልቃ መግባት ሲሆን ይህ ኃላፊነቱም አይደለም፤›› በማለት የሚያስረዱት አቶ አወል፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በተሰጠው ኃላፊነት ላይ ብቻ ምን ሠራህ መባል አለበት ይላሉ፡፡

አቶ አወል ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ዕርምጃ አለመወሰዱ ዋና የፍትሕ ሥርዓቱ እንቅፋት መሆኑን ከመናገር ባለፈም፣ የፍትሕ ሚኒስቴር በራሱ በኩል የተሰጠውን ሚና በሚፈለገው ልክ ለመፈጸም የአቅሙን ያህል መጣሩን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ዓመታት እውነቱን ለመናገር ያለ ዕረፍት እየሠራ ነው ያለው፡፡ በተለይ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት በእጅጉ በሥራ የተወጠረ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ወንጀል በመመርመር በኩል በየክልሉ ዞረናል፡፡ የሥራ ክፍሉ ያሉት 30 እና 40 አቃብያነ ሕጎች አልበቃ ብለው ከሌላ የሥራ ክፍሎች ጭምር ሙያተኞች እያመጣን ነው የሥራ ጫናውን ስንሸፍን የነበረው፡፡ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በዘጠኝ የምርመራ አካባቢዎች ብዙ ቁጥር ያላቸው አቃቤያነ ሕጎቻችን በተደጋጋሚ ተጉዘዋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብዙ ሺሕ ምስክሮችን አናግረዋል፡፡ የሰነድና የፎቶ መረጃዎችን አሰባስበዋል፡፡ ይህ ሁሉ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ ግን ቤኒሻንጉል ወይ ሌላ ቦታ ሌላ አዲስ ችግር መፈጠሩ ይሰማል፡፡ ይህን ሁሉ እየተዘዋወሩ መመርመር፣ አጣርቶ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍትሕ እንዲያገኝ ማደረግ ደግሞ ዞሮ የእኛው ኃላፊነት ነው የሚሆነው፡፡

‹‹አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አዲስ ዓይነትና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ መፍትሔዎችን ለማሰብም ፋታ የማይሰጥ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ጉልበተኞች ተደራጅተው ወንጀል የሚፈጽሙበት ሁኔታ በመስፋፋቱ፣ ዘላቂ መፍትሔና ስትራቴጂ ነድፎ ለመሥራት ፋታ አሳጥቶናል፡፡ እሳት የማጥፋት ነው ሥራችን፤›› በማለት የሚያስረዱት አቶ አወል፣ ተጨባጩ ችግር እንደ አገር ሰፊና ውስብስብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህ የፍትሕ ሚኒስቴር ሐሳብም ሆነ በመንግሥት የሚሰጡ ሌሎች ምክንያቶች የማያሳምናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ግን በርካታ ናቸው፡፡ ራሳቸው በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለረዥም ጊዜ የሠሩት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ ከእነዚህ አንዱ ሲሆኑ፣ ሥርዓተ አልበኝነትን በማስወገድ የሕግ የበላይነትን የማፅናት ጉዳይ ምክንያት ሊደረደርበት የማይችል የመንግሥት ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ያሳስባሉ፡፡

‹‹ሕገወጦቹ ከመነሻው ለወንጀል ሲዘጋጁ፣ ሲደራጁና ዕቅድ ሲያወጡ እየታየ ምንም አይደረግም፡፡ ወንጀል ፈጽመው እጃቸውን ኪሳቸው ከተው ሲንፏለሉም ምንም አይደረጉም፡፡ ስለሕግ የበላይነት እኛ አገር ማውራት ቅንጦት ሆኖብናል፡፡ መንግሥት የችግሮች ምንጭ የሆነውን የፌዴራል ሥርዓትና የጎሳ ፖለቲካ ታቅፎ መተኛትን መርጧል፡፡

‹‹አገሪቱን ይመራሉ የሚባሉ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ የሚናገሩት ግጭት ቀስቃሽ ነው፡፡ በንግግሮቻቸው ጠብ ቀስቃሽ ጉዳይ የሚከቱት ሆን ብሎ ግጭትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ አልመው ነው፡፡ እኛ አሁን እሳት እየነደደብን ያለው እኮ በትንንሽ ንግግሮች ነው፡፡ አንድ ባለሥልጣን ወይም አክቲቪስትና ፖለቲከኛ የሆነች ነገር በተነፈሰ ወይም አንድ አካባቢን ደጋግሞ ከጎበኘ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ሁሉ እስከ መገመት ደርሰናል፡፡ ነገርየው ከድግግሞሽ አልፎ ወጥ የሆነ ማሳያ ይመስላል፡፡

‹‹እንደምናየው ከሆነ አገሪቱን በሰላም ለመምራት መሪዎቹ ምንም ዝግጁነት የላቸውም፡፡ እኛም በዝምታ ሲኦል ለመግባት ዝግጁ የሆንን ይመስላል፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅድ እያጣን ዛሬን ማደር ብርቅ እየሆነብን ነው፤›› ሲሉ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ፣ ሆን ተብሎ ሥርዓተ አልበኝነቱን የመልቀቅና ዓይቶ እንዳላየ የመሆን ችግር በአገሪቱ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በአገሪቱ ስለሚታየው ሥርዓተ አልበኝነትና የሕግ የበላይነት መጓደል በብዙ አጋጣሚዎች ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተው ያውቃሉ፡፡ ከለገጣፎ ቤት መፍረስና የነዋሪዎች መፈናቀል ጀምሮ፣ የቡራዩ ግድያ፣ ከጃዋር መሐመድ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ነውጥ፣ የሐዋሳ ብጥብጥ፣ የአሶሳ ረብሻ፣ የጥምቀት በዓላት ሁከቶች፣ የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና ያስከተለው ረብሻ፣ የቤኒሻንጉል  ጉሙዝ ክልል ቀውስ፣ እንዲሁም የወለጋና የጉጂ ግጭቶች በሙሉ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን የተፈጠሩ ቀውሶች ናቸው፡፡ የሥልጣን ዘመናቸውን በሶማሌ ክልል ቀውስ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በጌዴኦ ጥቃት፣ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት ግድያ፣ በሰሜን ሸዋ ቀውስ፣ በትግራይ ጦርነትና በሌሎችም ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ያስከተሉ ችግሮችን በኃላፊነት በቆዩባቸው አራት ዓመታት ዓይተዋል፡፡

በእነዚህ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ስለችግሩ ተጠይቀው የሚያውቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚቀጥል ችግር መሆኑን ደጋግመው አመልክተዋል፡፡ የተዘጋ ቤት ከረዥም ጊዜ በኋላ ሲከፈት መጥፎ ጠረን እንደሚፈጥር በአንድ ወቅት የጠቀሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ችግሩ ለረዥም ዘመን በተዘራ የጥላቻ መርዝ የሚፈጠር መሆኑንና ይህ እስኪቀረፍም የሚቀጥል መሆኑን አስረድተው ያውቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት በአገሪቱ 113 ዋና ዋና የሚባሉ የሰው ሕይወት የቀጠፉና ንብረት ያወደሙ ግጭቶች መከሰታቸውን ለፓርላማው ሲያቀርቡ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥታቸው የማያዳግም ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ቃል ገብተውም ነበር፡፡

ነገር ግን የፀጥታ ችግሮቹ አሁንም ድረስ መቆም አልቻሉም፡፡ አንዳንዴ በረድ የማለት ዝንባሌ ቢኖራቸውም መልካቸውን እየለዋወጡ መቀጠላቸውን ከሰሞኑ የተፈጠሩ ሁከቶች ያረጋግጣሉ፡፡ እነዚህ ሁከቶች አሁን አሁን የሃይማኖት መልክ ይዘው መምጣታቸው ደግሞ ብዙዎችን እንደሚያሳስብ ነው እየተነገረ ያለው፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር ጉዳዩ እንደሚያሳስበው የሚናገሩት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አወል፣ ሆኖም ሚኒስቴሩ ብቻውን የፈለገውን ያህል ቢጥር ሰላምና ፍትሕ በመላ አገሪቱ ሊረጋገጥ እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ ለአንድ አገር ሰላም መስፈንና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ፍትሕ ሚኒስቴር አንዱ ተዋናይ እንጂ፣ ብቸኛው ባለድርሻ አለመሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ ያወሱት አቶ አወል ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ የፀጥታ መዋቅሩ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ማኅበረሰቡና በየደረጃው ያሉ አካላት የሚጫወቱት ሚናም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በአገሪቱ አሁን ያለው ሁኔታ አስጨናቂ ነው፡፡ የጎበዝ አለቅነት፣ ኃይለኝነትና ጉልበተኝነት እየሰፋ የሕግ የበላይነት እየተዳከመ የታየበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጥላቻን በመጠቀም ኃይል ያላቸው ሰዎች በማኅበረሰቡ ላይ ሁከት የሚፈጥሩበት ሁኔታ ጎልብቷል፡፡ ነገር ግን ሥርዓት አልበኝነቱ መቀረፍ የሚችለው ከክልል (ከታች) ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የፍትሕ አካላት ተሳትፎ ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር በዋናነት አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ ነው ሥራውን የሚሠራው፡፡ ክልሎች የራሳቸው ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ በራሳቸው ፖሊስ፣ በራሳቸው ፍርድ ቤትና በራሳቸው የፀጥታ መዋቅር ችግሮችን ይፈታሉ የሚል ዕሳቤ ነው ያለው፡፡ ክልሎች ራሳቸው በሚያስተዳድሩት አካባቢ ሰላምና ፀጥታን የማረጋገጥ ሥራ የራሳቸው መሆኑን በሚገባ ተገንዝበው ለዚህ የሚያግዝ ዕቅድና ስትራቴጂ ቀርፀው ሥራቸውን በአግባቡ ቢሠሩ ኖሮ፣ አሁን የተፈጠሩ የፀጥታ ቀውሶች የማይፈጠሩበት ወይም በዚህ ደረጃ የማይሰፉበት ዕድል ነበር ብለን እናምናለን፤›› ሲሉ አቶ አወል፣ በየድርሻው ያሉ አካላት ኃላፊነትን መወጣትና ከፌዴራል ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ግጭቶች አንዳንዴ በረድ የማለት አዝማሚያ ቢያሳዩም፣ ነገር ግን ባለፉት አራት ዓመታት ይብዛም ይነስ አገሪቱ ከግጭት አዙሪት ወጥታ አታውቅም የሚለው ነው ብዙዎችን የሚያስማማው፡፡ የትግራይ ክልል ጦርነት በተለይ በሕወሓት ኃይል ላይ ከባድ የሚባል ዕርምጃ መወሰዱ ለብዙዎቹ የግጭት ችግሮች መፍትሔ እንደሚያመጣ ቢገመትም፣ ነገር ግን አሁንም ድረስ አገሪቱ ከግጭትና ሁከት አለመላቀቋን ነው የቅርብ ሰሞኖቹ የጎንደር፣ የወራቤና የአዲስ አበባ ሁከቶች ያረጋገጡት፡፡ አሁን ሁኔታው ገጹን ቀይሮ ከብሔር ወይም ከቀዬ ወጥቶ የሃይማኖት መልክ ተላብሶ መምጣቱ ደግሞ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳሰበና ወዴት ልናመራ ነው የሚል ሥጋት እያሳደረ ነው፡፡

የሕግ ባለሙያው መንግሥቱ ሁኔታው ከፍ ያለ ሥጋት ይዞ መምጣቱን ይከራከራሉ፡፡ የግጭት አዙሪቱ የሚፈለግ ግብ ያለው ሲሆን፣ እሱም አገር ማፍረስ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹እኛ እኮ ስለኑሮ ውድነት እንኳ አላጉረመረምንም፡፡ የኑሮ ውድነትን ማማረር ቅንጦት ሆኖብን እሱን ችለን ማደርን አሜን ብለናል፡፡ አገር ከምትገኝበት ማጥ ውስጥ እስክትወጣ ሁሉንም ችለን እንለፈው በሚል ችለን ዝም ብለን እየኖርን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ችለን የምናልፈው ነው ወይ ስንል ሁኔታው በእኔ ግምት አይደለም፡፡ ለእኔ የሚታየኝ አሁን አገርን ማፍረስ ነው የተያያዝነው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወት እንደምናየው የሰዎች ፊት ላይ የመኖር ወይም የተስፋ ገጽታ አይታይም፡፡ ተስፋ መቁረጥ ሁሉም ዘንድ ይነበባል፡፡ ቤት መሥራት፣ ፋብሪካ መገንባት ቀርቶ ከአዲስ አበባ አሥር ኪሎ ሜትሮች ርቆ መሄድም የሚታሰብበት ሁኔታ የለም፡፡ ቀውሱ የፈጠረው ሥጋት ተጋብቶብናል፡፡ የባንክ አካውንታችን ውስጥ ገንዘብ አስገብተን ለምንፈልገው ነገር ማውጣት እንኳ ከብዶብናል፡፡

‹‹የሕግ የበላይነት መጥፋቱና ሥርዓተ አልበኝነቱ ያልነጠቀን ነገር የለም፡፡ ኑሮና ሕይወታችንን ቀምቶናል፡፡ መጀመርያ ራሳችን ድጋፍና ጭብጨባ በመስጠት ነው ወደ እዚህ ምስቅልቅል የገባነው፡፡ አሁን ደግሞ ሥጋትና ፍርኃት ተጭኖብናል፡፡ ወደፊት ደግሞ ምንም ውስብስብ ሒሳብ ሳንሠራ መገመት እንደሚቻለው አገሪቱ ወደ ከባድ አደጋና ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ወደ የማንወጣው ከባድ አደጋና ወደ አገር መፍረስ እየገባን ነው፤›› ሲሉ የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው ሲያክሉም አገሪቱ ወደ መፍረስ እየሄደች አይደለም የሚል ካለ እሱ አስመሳይና ክፉ ሰው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ያለንበትን አደጋ ለመሸፋፈን የሚጥርና አገሪቱን ለማፍረስ ያደባ ኃይል ነው ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› እያለ የሚደልለን፤›› የሚሉት አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹ችግሩ አገር እንዳያሳጣን መሥጋት እንደሚኖርብን ነው የሚያሳየን፤›› ብለው ‹‹አሁን ያለንበትን ችግር ለማቃለል መሞከርም ሆነ የሕግ የበላይነት ወይም ፍትሕና ወንጀል መከላከል በሚል ሰምና ወርቅ ተሸፋፍኖ መቅረብ ተገቢ አይደለም፤›› በማለትም ነው የሕግ ባለሙያው ሁሉም ለአገሩ አስቦ ለሕግ ተገዥ እንዲሆን ያሳሰቡት፡፡