የኦፌኮ መግለጫ የሃሰትና መሰረተቢስ ነው፤ በፍኖተ ሰላም የተቃጠለ መስኪድ የለም ።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) “በፍኖተ ሰላም ከተማ መስጊዶች ተቃጥለዋል” በሚል ያሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን የፍኖተ ሰላም መስጊድ ሰለም ምክትል ኢማም ሸህ ኢንድሪስ ኢማም ገለጹ፡፡

የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር የእስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች በደስታና በሀዘን የማይለያዩ፣ መስጊዶችንና አብያተ ክርስቲያናትን በጋራ የሚገነቡ የዳበረ የመረዳዳት እሴት ያላቸው መሆኑን በከተማ አስተዳደሩ የፍኖተ ሰላም መስጊድ ሰላም ምክትል ኢማም ሸህ ኢንድሪስ ኢማም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኢማሙ ኦፌኮ በፍኖተ ሰላም ከተማ መስጊዶች ተቃጠሉና ኢድ በሰላም አልተከበረም በሚል ያሰራጨው መረጃ በሀሰት የፖለቲካ ሴራ በእስልምና እና ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ ሀገር ለማፍረስ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ በመሆኑ መንግሥት ተከታትሎ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

የፍኖተ ሰላም ከተማ የእስልምና እና ክርስትና እምነት ተከታዮች በደስታና በሀዘን የማይለያዩ፣ መስጊዶችንና አብያተ ክርስቲያናትን በጋራ የሚገነቡ የዳበረ የመረዳዳት እሴት ያላቸው በመሆናቸው ኦፌኮ ስህተተቱን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበትም ምክትል ኢማሙ ተናግረዋል፡፡

በሀሰት የፖለቲካ ሴራ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስበርስ ግጭት በመቀስቀስ ሀገር ለማፍረስ የሚሞክሩ አካላት ፍላጎታቸው እንደማይሳካ ሸህ ኢንድሪስ ኢማም አሳስበዋል፡፡

ምክትል ኢማሙ እንደገለፁት የሁለቱም ቤተ እምነቶች አስተምህሮ እርስ በርሳችን እንድንጎዳዳ፣ እንድንዘራረፍና እንድንደማማ ሳይሆን በወንድማማችነት በመደጋፍ በእኩልነት እንድንኖር በመሆኑ ይህ የመረዳዳት አሴት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ዳውድ ሁሴን አስተያየታቸውን የሰጡን ሲሆን ከበፊቱ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢድ ሰላትን በሰላም ሰግደው ወደየቤታቸው መመለሳቸውንና በመስጊዱም ላይ ምንም አይነት ጉዳትና የፀጥታ ችግር አለመፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በግጭት የሚገኝ ጥቅም የለም ያሉት አስተያየት ሰጭው ኦፌኮ ያሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ድብቅ የፖለቲካ ተልዕኮ ያለው መረጃ በመሆኑ መንግሥት የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ አካላትን ተከታትሎ የማያዳግም እንምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ከክርስት እምነት ተከታዮች መካከል ወጣት አንተነህ ጥላሁን በበኩሉ የፍኖተ ሰላም ህዝበ ክርስቲያ ከሕዝበ ሙስሊሙ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው በእድር፣ በእቁብ፣ በደስታና በሀዘን ሁሉ የሚደጋገፍና የእምነት ተቋማትን በጋራ የሚገነባ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወጣት አንተነህ አክሎም የኦፌኮ መግለጫ ከእውነት የራቀ የሀሰት መረጃ በመሆኑ ወጣቶች የሀሰት መረጃዎችን በማጣራት ድብቅ የፖለቲካ እሳቤያቸው ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ተልዕኮ ማክሸፍ እንዳለባቸው
ገልጾ ኦፌኮ ለለቀቀው የሀሰት መረጃ ይቅርታ እንዲጠይቅና መንግሥትም በኦፌኮ ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ኃፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘገባው የምእራብ ጎጃም መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ነው።