“በጎንደር በደረሰው ጉዳት ከልብ አዝነናል፣ አጥፊዎች በአሰቸኳይ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን!” ሲል ባልደራስ በጎንደር የተከሰተውን አሳዛኝ ክስተት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የባልደራስ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡
በጎንደር በደረሰው ጉዳት ከልብ አዝነናል፣ አጥፊዎች በአሰቸኳይ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን!
/
በአማራ ክልል፣ ጎንደር ከተማ ሚያዝያ 17/2014 ዓ/ም ከሰዓት ከቀብር ስነ ስርዓት አፈፃፀም ጋር በተያየዘ የተነሳ ግጭት በርካታ አማኞች በመሞታቸው፣ መስጂዶች በመቃጠላቸው፣ ግለሶቦች እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ባልደራስ ፓርቲ በእጅጉ አዝኗል።
የችግሩ መነሻ ምንም ይሁን ምን፣ የተፈፀመው ነገር በፍጱም ሊወገዝ የሚገባ ነው፤ በተለይም የእምነት ተቋማት እና አማኞች ላይ የደረሰው ጥቃት አሳዛኝ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ሙስሊምና ክርስቲያን አማሮች ያለ ምንም ልዩነት በጋራ በሚጨፈጨፉበት፣ በሚፈናቀሉበትና የጋራ መከራ በሚቀበሉበት በዚህ ግዜ፣ እንዲሁም ሚሊዮኖች የእለት ደራሽ ምግብ በአጡበት ክልል እንዲህ ዓይነት ችግር መፈጠሩ በእጅጉ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው።
ግጭቱ እንዳይሰፋና የፀረ-ኢትዮጰያ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን፣ የሚመለከታቸው የክልሉ የፍትህ አካላት፣ የእምነት አባቶች እና ተፅእኖ ፈጣሪዎች በሙሉ በአስቸኳይ የተቀናጀ እንቅስቃሴ አድርገው የከተማውን ፀጥታ ለማስጠበቅ መረባረብ አለባቸው።
በከተማዋ ነዋሪ በኩል፣ በግጭቱና በደረሰው ጉዳት እጃቸው ያለበትን አካላት ያለምንም ይሉኝታ ለሕግ አሳልፎ በመስጠት ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ይገባቸዋል። በቀጣይነት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መመካከር እንደሚያስፈልግ ባልደራስ ያምናል።
በስተመጨረሻም፣ በዚህ ችግር የሞቱትን ፈጣሪ ነፍሳቸውን እንዲቀበል፣ ወዳጆቻቸውን ላጡ ፈጣሪ መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን።
እናት ዓለም ኢትዮጰያ ክፉሽን አያሳየን!!!