ለፓርላማው ከሁለት ዓመት በፊት የቀረበን ሪፖርት በቀጥታ ገልብጦ ያቀረበው የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር” እጅግ ነውር ተግባር” ፈጽሟል ተባለ

[addtoany]

አሳፋሪው ሚኒስትር የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከሁለት አመት በፊት በተዘጋጀ የዶክተር ስለሺ በቀለ ሪፖርት ፓርላማውን ለማጭበርበር ሲሞክር ተደርሶበት በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ተወግዟል። ይህ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት በተደጋጋሚ በሚኒስትሮች እየታየ ሲሆን የአብይ አሕመድ ካቢኔ የሃሰት ሪፖርት በሚያቀርቡ ሚኒስትሮች የተሞላ መሆኑ ሲታወቅ ከዛ በባሰ መልኩ የድሮ ሪፖርቶችን ደግሞ በማቅረብ ፓርላማውን እያታለሉ ነው። ከተለያዩ ሚዲያዎች የተገኙ ዘገባዎችን ከታች ያገኙታል።

ከሁለት ዓመት በፊት የቀረበን ሪፖርት በቀጥታ ገልብጦ ያቀረበው የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር” እጅግ ነውር ተግባር” ፈጽሟል ሲል ቋሚ ኮሚቴውን ገለጸ

የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርብ በተገኘበት መድረክ ምንም ዓይነት የሪፖርት ማሻሻያ ሳያደርግ በቀጥታ እየገለበጠ እንደሚያስተላልፍ ደርሼበታለዉ ሲል የዉሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አከባቢ እና አከባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

ቋሚ ኮሚቴ የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ባደመጠበት ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርቶችን በቀጥታ ገልብጦ ከማምጣቱም ባሻገር የተቋሙ የበላይ ሃላፊዎች የማያዉቁት እና ያልተገመገመ ሪፖርት ለ ምክርቤት መላኩ እጅግ ነዉር ነዉ ሲል ቋሚ ኮሚቴዉ ወቅሷል፡፡

ሪፖርቱ በ ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካለንበት 2014 የግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርቶች በቀጥታ ተገልብጠዉ የተላለፉ ናቸዉ ብሏል ቋሚ ኮሚቴዉ፡፡
ለማሳያነትም በስነምግባር እና ጸረ ሙስና ብልሹ አሰራሮች ናቸዉ ተብለዉ ከቀረቡት 16 ጥቆማዎች መሀል 13ቱ ተጣርተዉ መልስ የተሰጣቸዉ ሲሆኑ 3 ጥቆማዎች በሂደት ላይ የሚገኙ ናቸዉ የሚለዉ አፈጻጸም ከ 2012 የዘጠኝ ወር ሪፖርት ቃል በቃል ምንም ለዉጥ ሳይደረግበት ተገልብጦ የመጣ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፣ ይህንንም ሀሰት ነዉ የሚል አካል ካለ በርካታ ተጨባጭ የሰነድ ማሳያዎች ማቅረብ እንችላለን ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፈትያ አህመድ ተናግዋል፡፡

በሚኒስቴር ዲዔታ ማዕረግ የሚኒስቴሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ በሪፖርቱ ላይ የቀረበዉ ትችት ትክክል እንደሆነ አምነዉ የሪፖርት ጥራትና ወቅታዊነት ጉዳይ በፍጹም ለጥያቄም ቢሆን የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ አንስተዉ መስተካከል እንዳለበት እንደሚያምኑ እና የተለያዩ መስሪያ ቤቶች አንድ ላይ መዋሃድ ይህንን ክፍተት መፍጠሩን እንደምክንያት ያነሱ ሲሆን በቀጣይ ይህንን አስተካክለዉ እንደሚቀርቡ ገልጸዉ ፣ ቋሚ ኮሚቴዉን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ዘገባው የኢትዮ ኤፍ ኤም ነው።

የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ይህን ያስታወቀው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ዛሬ አርብ ሚያዚያ 7፤ 2014 በገመገመበት ወቅት ነው። በቋሚ ኮሚቴው ግምገማ መሰረት፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘንድሮ የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለፓርላማ ያስተላለፈው ከ2012 የአፈጻጸም ሪፖርቶች “በቀጥታ በመገልበጥ” ነው።

የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ እሱባለው መብራቴ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “የበላይ ኃላፊዎች የማያውቁት እና ያልተገመገመ ሪፖርት” ለተወካዮች ምክር ቤት መላኩን በዛሬው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ መደገሙን ያወቁት በአጋጣሚ እንደነበር አቶ አለሙ ጌታሁን የተባሉ የፓርላማ አባል ገልጸዋል።

“ወደዚያ የሄድነው ችግር ፍለጋ አልነበረም። የቁጥጥር እና ክትትል ስራ በምክር ቤቱ ተሰጥቶናል። ተቋሙ ገብቶን ልንቆጣጠር ይገባል ብለን፤ የኋላ አፈጻጸሙን በተለይ የፕሮጀክት አፈጻጸሙ ላይ ‘ምንድን ነው ያለው ነገር? 2012 ምን ይመስላል?’ ብለን ከዚያ ተነሳን። የዘጠኝ ወር ሪፖርቱን ስናነብ ቆይተን ስለነበር የ2012ን [ሪፖርት] ስናነብ፤ የዘጠኝ ወር ላይ ያገኘነውን ነገር 2012 ላይ አገኘን” ሲሉ በንጽጽራቸው የደረሱበትን መደምደሚያ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች አብራርተዋል።

አቶ አለሙ ሪፖርቱ መደገሙን በማሳያዎች ጭምር አስደግፈው አስረድተዋል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት የ2014 ዕቅድ አፈጻጸም ከሁለት ዓመታት በፊት በ2012 ከነበረው የዕቅድ አፈጻጸም ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ ተመሳሳይ አካሄድ በሌሎቹ የሪፖርቱ ክፍሎች መታየቱንም አመልክተዋል።

የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉ “ብልሹ አሰራሮችን” በመለየት ያሳወቀበት እና ለዚሁ ችግር የሰጠውን ምላሽ የሚያሳየው የሪፖርቱን ክፍል ሌላኛው የቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ እሱባለው በማስረጃነት ጠቅሰዋል። የኮሚሽኑ ገለጻ እና ምላሽ “አንድም ፊደል ሳይጨመር እና ሳይቀነስ እንዳለ ከ2012 የዘጠኝ ወር ሪፖርት ተገልብጦ የመጣ” መሆኑን የፓርላማ አባሉ በንባብ ባሰሙት ግምገማ ላይ ተገልጿል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ወክለው በቋሚ ኮሚቴው ሰብሰባ ላይ የተገኙት የተቋሙ አመራሮች ችግሩ መከሰቱን አምነዋል። ለፓርላማ የሚላኩ ሪፖርቶች በከፍተኛ አመራሮች እንደሚገመገሙ የሚገልጹት አመራሮቹ፤ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ለቋሚ ኮሚቴው የተላከውን ሪፖርት አለመገምገማቸውንም ተናግረዋል።

የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ሱልጣን ወሊ “ይኼ ሪፖርት በሚላክበት ወቅት ሁሉም [አመራሮች] ከሚኒስትሩ ጀምሮ ሚኒስትር ዲኤታዎችን ጭምር፤ የመስክ ስራዎች ላይ ስለነበርን ሪፖርቱን ሳንገመግም እና ሳናይ ነው የላክነው” ብለዋል።

የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር አብርሃም አዱኛ “ሪፖርት እንድናቀርብ የተጠየቅነው ባለፈው ረቡዕ ቀን ነበር። ረቡዕ ደርሶ በአስቸኳይ አመራሩም ሳያየው የተላከ ነው” ሲሉ ለችግሩ መከሰት አንደኛው ምክንያት የጊዜ እጥረት መሆኑን ገልጸዋል። በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ “ቀኑን ለመጠበቅ ተብሎ አንዳንድ ጊዜ ጥራት የሌለው ሪፖርት ይላካል” ሲሉ ሪፖርቱ መደገሙን ለቋሚ ኮሚቴው አረጋግጠዋል።

በአዲሱ የመንግስት አደረጃጀት መሰረት የተለያዩ መስሪያ ቤቶች እንዲዋሃዱ መደረጋቸውን እና ይህም በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ላይ መተግበሩ በእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ ችግር ለመፈጠሩ በተጨማሪ ምክንያትነት ተነስቷል። ዶ/ር ሱልጣን ወሊ ችግሩ የተከሰተው “የተለያዩ ተቋማት ስለተዋሃዱ” መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ሲገልጹ፤ አቶ ሞቱማ በበኩላቸው “ከመስሪያ ቤቶቹ ወደ አንድ መዋሃድ ጀምሮ ክፍተቶች አሉ” ሲሉ የሚኒስትር ዲኤታውን ሃሳብ አጠናክረዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቀድሞ ስሙን የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመተው እንደ አዲስ የተዋቀረው ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ነበር። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ መልክ ሲዋቀር የሶስት የመንግስት መስሪያ ቤቶች መብት እና ግዴታዎች ተሰጥተውታል።

መብት እና ግዴታቸው ወደ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተላለፉት መስሪያ ቤቶች መካከል ከሶስት ዓመታት በፊት በ2011 ዓ.ም የተቋቋሙት የውሃ ልማት ኮሚሽን እና የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ይገኙበታል። የ20 ዓመታት እድሜ ያለው የውሃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤትም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር እንዲሆን ተደርጓል።

“በጊዜ እጥረት እና በመስሪያ ቤቶች መዋሃድ” ምክንያት ተፈጠረ የተባለው የሪፖርት መደገም ችግር ከታወቀ በኋላ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማስተካከያ ለማድረግ መሞከሩን የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር አብርሃም ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል። መስሪያ ቤታቸው “ችግር ያለበትን ሪፖርት” አስተካክሎ ለቋሚ ኮሚቴው በትላንትናው ዕለት መላኩንም ገልጸዋል።

በተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አወቀ አምዛዬ፤ የተስተካከለውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሪፖርት በትላንትናው ዕለት መቀበላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሆኖም ቋሚ ኮሚቴው የተስተካከለውን ሪፖርት ለመመልከት በድጋሚ ለስብሰባ እንደማይቀመጥ ገልጸዋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ከዚህ በኋላ የሚታየው በተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መሆኑን የቋሚ ኮሚቲው ምክትል ሰብሳቢ አስረድተዋል። ሪፖርቱ ለፓርላማው ከመላኩ በፊት ግን ቋሚ ኮሚቴው በሰጣቸው አስተያየቶች መሰረት መስተካከሉን እንደሚያረጋግጥ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)