ከወደቦች ዕቃ ለመጫን በፊት ከነበረው ዋጋ እስከ ስድስት ዕጥፍ ጭማሪ መደረጉ የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ ፈተና ላይ ጥሎታል

የመርከብ የዕቃ ማጓጓዣ ላይ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ ፈተና ላይ ጥሎታል

ዋዜማ ራዲዮ– በዓለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው የመርከብ የዕቃ ማጓጓዣ ዋጋ የኢትዮጵያ መርከቦችንም የታሪፍ ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ዋዜማ ራዲዮ የተመለከተችው አዲስ የመርከቦች የዕቃ ማጓጓዣ ተመን በምንዛሪ ዕጥረት፣ በዋጋ ግሽበትና ከጦርነት ጋር በተያያዘ የተዳከመውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚፈታተን አዲስ አደጋ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ካዘጋጀው ባለ 15 ገጽ ሰነድ እንደተረዳነው ከአንዳንድ ወደቦች ዕቃ ለመጫን በፊት ከነበረው ዋጋ እስከ ስድስት ዕጥፍ ጭማሪ ተደርጓል።

እስካሁን ጥቅም ላይ የነበረው የምርቶች የመርከብ ማጓጓዥ ዋጋ ተመን በሰኔ 2012 አ.ም የወጣው ነበር።ከመጋቢት 26 2014 አ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው አዲሱ ተመን ደግሞ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ይፋ ሆኗል።

በርካታ የኢትዮጵያ አስመጭዎች ከሚጠቀሙት ከቻይና ሸንዘን ሼኩ ወደብ ለሚነሱ መርከቦች የተቀመጠው መጓጓዣ ታሪፍ ከፍተኛ ጭማሬ የታየበት ነው። በ2012 አ.ም ሰኔ ወር ላይ ወጥቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲያገለግል የነበረው ተመን ፤ ከዚህ ወደብ 12 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንቴነር (የዕቃ ማጓጓዣ የብረት ሳጥን) የተጫነ እቃን በመርከብ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማጓጓዝ የሚጠየቀው ዋጋ 1,750 የአሜሪካ ዶላር ነበር።

አሁን ተግባራዊ በተደረገው ተመን ደግሞ ከዚሁ ተመሳሳይ ወደብ እቃ የያዘ 12 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንቴነር በመርከብ አጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ ለማድረስ የተቀመጠው ዋጋ 11,935 የአሜሪካ ዶላር ነው። የዚህና ከአብዛኛው የቻይና ወደቦች በሚደረገው የመርከብ መጓጓዣ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሬ የተደረገባቸው መሆኑን የተመለከትነው የዋጋ መዘርዝር ያሳያል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካሉ ወደቦች በሚነሱ መርከቦች ላይም እንዲሁ የዋጋ ጭማሬ ተደርጓል።በርካታ የኢትዮጵያ አስመጪዎች ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደቦች ጀበል አሊ እና ሻርጃ ወደቦች የሚነሱ የኢትዮጵያ መርከቦችን  ይጠቀማሉ።

ከሻርጃ ወደብ በ2012 አ.ም 12 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንቴነር ለመጫን ዋጋው 2,260 ዶላር ሲሆን አሁን በወጣው ተመን ወደ 4,005 የአሜሪካ ዶላር ጨምሯል።

ከጀበል አሊ ወደብ ደግሞ 2,580 ዶላር የነበረው 12 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንቴነር ማጓጓዣ ዋጋ 4,665 ዶላር ሆኗል። እንዲሁም ከቱርክ ኢስታንቡል ወደብ 2,242 ዶላር የነበረው ማጓጓዣ 3,000 ዶላር ሆኗል።

ሶስቱ ሀገራት ብዙ የኢትዮጵያ የገቢ ምርቶች የሚመጡባቸው የሀገራት ወደቦች ሲሆኑ የመርከብ ማጓጓዣ ዋጋ የጨመሩባቸው ናቸው። በሌሎች ሀገራት ወደቦችም የመጓጓዣ ዋጋ ጭማሬ ታይቷል።

የአለም የባህር ትራንስፖርት ላይ የታየው ጭማሬ እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ በአለም የንግድ ስርአት  የተከሰተው የኮንቴነር እጥረትና የዋጋ ውድነትም ለማጓጓዣ ዋጋው ጭማሬ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

የዋጋ ጭማሬው ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ የዋጋ ንረት ያስከትላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የመርከብ ማጓጓዣ ዋጋ መጨመር የሚፈጥረው የምርቶች የዋጋ መናርም በሁለት ምክንያቶች አሉታዊ ጎኑ የከፋ ነው። አንዱ ፣ የመርከብ ዋጋ የጨመረው በሺህ በሚቆጠር ዶላሮች ብቻ ሳይሆን የብር የምንዛሬ ተመን በእጅጉ በተዳከመበት ወቅት በመሆኑ የሚፈጥረውን የዋጋ ንረት ከፍ ደርገዋል።

በሌላ በኩልም አስመጪዎች ሀገር ውስጥ ባለ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ በባንኮች አማካይነት ከምርት ላኪዎች ጋር በሚፈጥሩላቸው ትስስር ለአንድ የአሜሪካ ዶላር ከነኮሚሽኑ እስከ 70 ብር እየከፈሉ የምርት ማስመጫውን እና ማጓጓዣውን ስለሚከፍሉ ለእያንዳንዱ ምርት የሀገር ውስጥ ገበያ መሸጫ የሚጠይቁትን ዋጋ ያንረዋል።

የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከወራት ወዲህ ከ30 በመቶ በላይ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]