በሕገ መንግስቱ መሰረት ሸገር/ናዝሬት/ደራ/ፈንታሌ …አማራ ክልል መሆን ነበረባቸው #ግርማካሳ

[addtoany]
በ1986 ዓ/ም አሁን ያለው፣ የሕወሃትና የኦነግ የአሸናፊዎች ሕገ መንግስት ከመጽደቁ በፊት የሕዝብ ቆጠራ ተደርጎ ነበር፡፡ የሕዝቡ ቆጠራውን ያደረገው የስታቲስቲካል ኤጀንሲ ሲሆን፣ ተቋሙ እንደሌሎች ተቋሞች በሕወሃትና በኦሮሞ ፖለቲከኞች ተጽኖ ሰር ወድቆ የነበረ መሆኑን የሚታወቅ ነው፡፡ ሕወሃቶችና የኦሮሞ ድርጅቶች፣ ሆን ብለው የዘር ፖለቲካቸውን ሊቃወሙ የሚችሉትን ማሀረሰባት ቁጥራቸው እንዲያንስ ማድረጋቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በሕወሃት ጊዜ የተደረጉ የሕዝብ ቆጠራዎች ሙሉ ለሙሉ ትክክል ነበሩ ብሎ መናገር አይቻልም፡፡
እንደዚያም ሆኖ ግን ያለው ብቸኛው ኦፌሴላዊ ሪፖርት እርሱ እስከሆነ ድረስ፣ እስከነ ችግሩ ልንጠቀምበት የምንችለው ሪፖርት እርሱን ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በታች ለቀረበው ጽሁፍ የ1986 የሕዝብ ቆጠራ ሪፖርት እንደ ምንጭ ቀርቧል፡፡
የሕወሃት/ኦነግ ሕገ መንግስት በአንቀጽ አንቀጽ 46 ስለፌዴራል ክልሎች አመሰራረት ያስቀምጥና፣ በአንቀጽ 47፣ በአንቀጽ 46 መሰረት የተመሰረቱ ክልሎችን ያላቸውን ይዘረዝራል፡፡ አንቀጽ 46፣ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ እንደሚሆንና ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ እዚህ ጋር ልብ እንበል ሕገ መንግስቱ አራት መስፈርቶችን ነው ያስቀመጠው፣ የሕዝብ አሰፋፈር፣ ማንነት፣ ቋንቋና የሕዝብ ፍቃድ ናቸው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ሰሜን ሸዋ ዞኖች እንዲሁም አዲስ አበባን ለናሙና ያህል ስንመለከት በአንቀጽ 47 ላይ የተመሰረቱት ክልሎች አንቀጾ 46 ላይ ያለውን መስፈርት ራሱ ያላከበሩ መሆናቸውን ነው እናያለን፡፡
ቋንቋና ማንነት አንዱ መስፈርት ነው፡፡ በ1986 የሕዝብ ቆጠራ መሰረት የደራ፣ እነ ፍቼ፣ ደብረ ሊባኖስ ያሉበት የግራር ጃርሶ ፣ እንዲሁም ዋና ከተማው መተሃራ የሆነው የፈንታሌ እና አዳማ ከተማ፣ ሶደሬ ፣ ወንጂ የመሳሰሉትን የሚጨምረው የአዳማ ወረዳዎች፣ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ወይም ኦሮሞዎች አብላጫ ያልሆኑባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
የአዳማ ወረዳ ነዋሪዎች ከተሞቹንና ገጠሮቹን ጨምረን 55% ነዋሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ የሆኑት 35% ብቻ ናቸው፡፡ ታዲያ ከአማራ ክልል ጋር የሚገናኘው የአዳማ ወረዳ በሕገ መንግስቱ አንቀሽ 46 መሰረት ወደ አማራ ክልል እንጂ ወደ ኦሮሞ ክልል መጠቃለል ነበረበት ?
እንደዚሁም የፈንታሌ ወረዳ ኦሮሞኛ የአፍ መፋቻ ቋንቋቸው የሆኑ 39% ናቸው፡፡ 61% የሚሆነው ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደለም፡፡ በደራና በግራር ጃሮስ ከ51% በላይ ነዋሪዉ አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ነው፡፡ ታዲያ ደራ፣ ግራር ጃርሶ፣ ፈንታሌ ወረዳዎች ወደ ኦሮሞ ክልል መጠቃለላቸው አንቀጽ 46 የሚቃረን አይደለም ወይ ?
የኦሮሞ ድርጅቶች እንዲሁም ገዢው የኦህዴድ/ብልጽግናን ጨምሮ፣ አንድ እየደጋገሙት የሚከራከሩበት ነገር ቢኖር አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፣ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሞ ክልል መጠቃለል አለባት የሚል ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስትም፣ በኦሮሚያ ሕገ መንግስት ውስጥ። ኢሕገመንግስታዊ በሆነ መልኩ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ ነው ብሎ ወስኖ፣ ጽ/ቤቱንም አዲስ አበባ ላይ አድርጓል፡፡
አዲስ አበባ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 መሰረት፣ 1ኛ የፌዴራል መስተዳደሩ ዋና ከተማ እንደሆነች፣ 2ኛ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት እንዳላት፣ 3ኛ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደምትወከል፣ 4ኛ የአዲስ አበባ መስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግስቱ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 5 ላይ ደግሞ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮችን በተመለከተ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እንደሚኖራት ያስቀምጣል፡፡ ሃረር ክልል በኦሮሚያ መሃከል፣ ሌሶቶ በደቡብ አፍሪካ መካከል እንዳሉት፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለች መሆኗን ህገ መንግስቱ ጠቅስ ማድረጉን እንደ ምክንያት በመቁጠር፣ ህገ መንግስቲ አዲስ አበባ በኦሮምኪያ ውስጥ ናት ያለ ይመስል፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል አድርገው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ማስቀመጣቸው አግባብነት የሌለው ብቻ ሳይሆን የማመዛዘንና የልጂክ ችግር ያለባቸው መሆን አመላካች ነው።
እዚህ ጋር ሶስት የሕገ መንግስት ተቃርኖዎች ለማየት እንሞክር፡
1ኛ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 8 መሰረት፣ “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው’ ስለሚል፣ የኢትዮጵያ ግዛቶች ባለቤት የሆኑት ብሄር ብሄረሰብና ሕዝቦች የሚባሉት ናቸው፡፡ በአንቀጽ 8 መሰረት ፣ አዲስ አበባ ለአንድ ወይንም ለብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መሰጠት ነበረባት፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር ለብቻዋ መመስረት አንቀጽ 8ን የሚሽር ነው፡፡
2ኛ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንዳለው ቢቀመጥም፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት እንዳለው አይገልጽም፡፡ የአዲስ አበባን ህዝብ እንደ አንድ “ብሄር ብሄረሰብና ህዝብ” አይቆጥረውም፡፡ በአንቀጽ 39፣ ንኡስ አንቀጽ 5 ላይ፣ ፡ብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ” የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ ትርጓሜ አስቀምጧል፡፡ “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ” ፣ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” ይላል፡፡ ይህ ተርጓሜ ራሱን ግራ ተጋብቶ ግራ የሚያጋባ በአንድ ትልቅ የህግ ሰነድ በዚህ መልኩ መቅረብ ያለበት ትርጓሜ አይደለም።
የአዲስ አበባ ህዝብ 72 የአፍ መፍቻ ቋንቋ አማርኛ ሲሆን፣ 25% እንደ ተደራቢ ቋንቋ አማርኛን ይናገራሉ፡፡ ሁለቱ ሲደመሩ 98% ወይ እንደ አፍ መፍቻ፣ አሊያም እንደተደራቢ ቋንቋ አማርኛን የሚናገሩ ናቸው፡፡ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚለውን መስፈርት የአዲስ አበባ ህዝብ ያሟላል፡፡
ተመሳሳይ ልምዶች፣ የስነ ልቦና አንድነት፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና ለሚሉት መስፈርቶች እንደውም በኦሮሞ ክልል ውስጥ ባሉ በአርሲዎችና በወለጋዎች፣ ወይንም በቦረናዎችና በቱሉማዎች መካከል የባህል ሆነ የልማድ ፣ የስነ ልቦና መቀራረብ ሳይኖር ነው በአንድ ክልል ውስጥ የተጠቃለሉት፡፡ አዲስ አበባ ስትመጡ ወላጆቻቸው፣ ወይም አያቶቻቸው ከትግራይ፣ ሃረር፣ ወለጋ የመጡ ቢሆኑም ልጆቻቸው የአዲስ አበባ ልጆች ነን ነው የሚሉት፡፡ እንደ አዲስ አበባ ነዋሪነታቸው ቤተሰቦቹ ከወለጋ የመጡ ወጣት፣ ቤተሰቦቹ ከመቀሌ ከመጡ የአዲስ አበባ ልጅ ጋር ነው የሚቀራረበው፡፡ ስለዚህ በአንቀጽ 39 ንኡስ አንቀጽ 5 መሰረት በተቀመጠው መስፈርት የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ “ብሄር ብሄረሰብን ህዝብ” ተቆጥሮ ክልል መሆን መቻል ነበረበት፡፡ አዲስ አበባ ምንም አይነት የፌዴራል status የሌላት፣ በአየር ላይ የምትንሳፈፍ፣ የኦሮሞ ድርጅቶች ቀዳዳ አግኘተው አዲስ አበባን ለመጠቅለል እየሰሩ ያሉትን በዋናነት በዚህ በአንቀጽ 39 እና በአንቀጽ 49 መካከል ባለው ተቃርኖ ምክንያት ነው።
3ኛ የአዲስ አበባ ህዝብ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት 73% የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ነው፡፡ ሌሎች 25% እንደተደራቢ ቋንቋ አማርኛን ይናገራሉ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 46 መሰረት፣ ቋንቋና ማንነት እንደ መስፈርት ከተወሰደ አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል መሆን ነበረባት፣ ወይንም በአማራ ክልል ውስጥ መካተተ ነበረበት፡፡
በአዲስ አበባና በአማራ ክልል መካክል በሬዓ፣ አለለቱና ጊምቢቹ የሚባሉ ወረዳዎች አሉ፡፡ በነዚህ ወረዳዎች ከ172 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 15% አማርኛ ተናጋሪዎች ሲሆኑ 85% ኦሮሞኛ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ወረዳ የሚኖሩ ኦሮሞኛ ተናጋሪዎች ብዙዎች አማርኛንም እንደተደራቢ ቋንቋ የሚናገሩ ናቸው፡፡ 170 ሺህ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ መካከል አሉ ተብሎ፣ ከ2 ሚሊዮን በላይ አማርኛ ተናጋሪ ያለባትን አዲስ አበባ ከአማራ ክልል መለየት በህገ መንግስቱ መሰረት ከወሰድነው ትክክለኛ አሰራር አይደለም፡፡
4ኛ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 46 መሰረት፣ ክልሎች ሲመሰረቱ አንዱ መስፈርት የሕዝብ አሰፋፈር ሲሆን፣ ሌላው የህዝብ ፍቃድ ነው፡፡ የህዝብ አሰፋፈር ሲባል ሕገ መንግስቱ ግልጽ አላደረገውም፡፡ አንድ ሕገ መንግስት ያለ ትልቅ ሰነድ፣ የአተረጓገም ችግር እንዳይከሰት፣ በግልጽ መጻፍ ነው ያለበት፡፡ ግን አሁን ባለው ሕገ መንግስት ብዙ ግልጽ ያልሆኑ አባባሎች አሉ፡፡
የሕዝብ ፍቃድን በተመለከተ፣ አሁን ያለው አከላለል ፣ በኦነጎችና በሕወሃቶች ተጽፎ በሕዝብ ላይ በጉልበት የተጫነ እንጂ ህዝብ ተጠይቆ የተዋቀረ አወቃቀር አይደለም፡፡ ህዝብ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እንዴት መካለል ትፈልጋለህ ተብሎ ፍቃዱ ቢጠየቅ ኖሮማ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ ፣ የደቡብ …የሚባሉ ክልሎች አይኖሩም ነበር፡፡
በአጠቃላይ አሁን ያለው በአንቀጽ 47 የተቀመጠው የጎሳ አከላለል፣ አንቀጽ 46ን፣ የአዲሳ አበባም ጉዳይን አንቀጽ 8ን የሚሽር ነው። በአንቀጽ 46 መሰረት አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ፈንታሌ፣ ግራር ጃርሶ፣ ደራ በአማራ ክልል ስር መሆን ነበረባቸው፡፡
ወደ ሃረር፣ ድሬዳዋ፣ ሞያሌ፣ ወልቃይት፣ ባቢሌ፣ ጉርሱም፣ ሜኢሲ፣ ሊበን፣ ራያ፣ ኬሚሴ፣ መተከል፣ አሶሳ …የመሳሰሉትን በርካታ አካባቢዎችም መጥቀስ ይችላል። በተለይም የሃረር ክልል አመሰራረት እጅግ በጣም አስቂኝ ነው። ምን ያህል ክልሎች የተመሰረቱበት አኳኋን እንድ ሕጻን ከሚያደርገው የጭቃ ማቡካት ጨዋታ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ይሄን ስል አዲስ አበባ፣ ናዝሬት ….በአማራ ክልል ስር ይሁኑ የሚል መከራከሪያ እያቀረብኩ አይደለም፡፡ አከላለሉ ምን ይህል እጅግ በጣም ትልቅ ግደፈት ያለበት መሆኑን ለማሳየት እንጂ። በኔ እይታ፣ የአማራ ክልል ራሱ መፍረስ አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ታሪካዊቷ ሸዋ መመስረት አለባት ባይ ነኝ፡፡ ምንጃር፣ ሸንኮራ፣ ደብረ ብርሃኑ ወዘተ በባህር ዳር ስር መሆናቸው ለአስተዳደር አመች አይደለም፡፡ የአማራ ክልል ፈርሶ፣ ሸዋ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር በሚል አነስ ወዳለ መስተዳደሮች መሸንሸን አለበት፡፡ ሸዋ ደግሞ በኦሮሞ ክልል ያሉ የሸዋ ዞኖችን አቅፎ፣ የአንድ ጎሳ ብቻ ሳይሆን ሕብረ ብሄራዊ መስተዳደር እንዲሆን መደረግ ነው ያለበት፡፡ አማርኛና ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ ሆኖ። የሸዋ ህዝብ አማራውም ሆነ ኦሮሞውም አንደኛ የስነ ልቦና አንድነት ነው። ሁለተኛ ቋንቋም ቢሆን ብዙ አማራዎች ኦሮምኛ ፣ ብዙ ኦሮሞዎች አማርኛ ያውቃሉ።፡ቋንቋ ጋር ችግር የለም። ሸዋ ያለው ህዝብ በቋንቋና በዘር ሳይከፋፈል፣ አንድ ላይ ሲቆም ታሪክ የሰራ ማህበረሰብ ነው። አሁንም አንድ ሆኖ ከመጣ ታሪክ ሊሰራ የሚችል ነው። ሸዋ የኢትዮጶያ፣ የኢትዮጵያዊነት መሰረት ነው። ወያኔዎች ሆነ ኦነጎች ሸዋ ተንካራ ሆኖ እንዲመጣ አይፈለጉም። ለምን ጠንካራ ኢትዮጵያውን ማየት ስለማይፈልጉ።